ባሕር ዳር፡ ጥር 27/2018 ዓ.ም (አሚኮ) ክርስቲያኖ ሮናልዶ ዶስ ሳንቶስ አቬይሮ ሙሉ መጠሪያ ስሙ ነው፡፡ ቅፅል ስሙ ደግሞ ሲ᎐ አር ᎐7 ነው፡፡ ይሁን እና ዓለም ”ክርስቲያኖ ሮናልዶ” በሚለው ስሙ ነው የሚያወቀው፡፡
ፖርቱጋላዊው ክርስቲያኖ ሮናልዶ እንደ አውሮፓ አቆጣጠር ከ2023 ጀምሮ የሳዑዲ አረቢያውን አል-ናስር ክለብ ተቀላቅሎ በ95 ጨዋታዎች በመሠለፍ 91 ግቦችን መረብ ላይ ማሳረፍ ችሏል፡፡
41ኛ ዓመቱን በቅርቡ የሚያከብረው ሮናልዶ በአንድ ወቅት ”የአል-ናስር ቡድን በሁሉም ነገሩ ልክ እንደምተኛበት ፍራሽ ተመችቶኛል” ማለቱ ይታዎሳል፡፡
ከሰሞኑ ግን በሮናልዶ እና በአል-ናስር መካከል አለመግባባት መፈጠሩ ተዘግቧል፡፡ ለዚህ ማሳያው ደግሞ አል-ናስር ሰኞ ዕለት በነበረው ወሳኝ ጨዋታ ተጫዋቹን አላሰለፈውም፡፡
ትናንት በነበረው የቡድኑ ልምምድ ላይም ሮናልዶ ”ኾን” ብሎ አልተገኘም፡፡ የስፖርት ቤተሰቡ እና በርካታ ተዋቂ የመገናኛ ተቋማትም የተለያዩ አስተያየቶችን ሲሰጡ ሰንብተዋል፡፡
ዛሬ ግን ዴይሊ ሜይል ስፖርት ተጫዋቹ የሳዑዲ አረቢያውን አል-ናስር ሊለቅ መኾኑን ዘግቧል፡፡
ሮናልዶ ” ከአል-ናስር ጋር ብቻ ሳይኾን በሳዑዲ አረቢያ በአጠቃላይ እስያ ውስጥ መጫወት አልፈልግም፤ ወደ አውሮፓ መመለስ ፈልጌያለሁ፤ ወይም ወደ አሜሪካው ሜጀር ሊግ ሶከር እሄዳለሁ” ማለቱን ዴይሊ ሜይል ስፖርት ጨምሮ አስነብቧል፡፡
በሙሉጌታ ሙጨ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!



