በእንግሊዝ ፕሪሚየር ሊግ “አየተሞገሰች ያለችው ዳኛ “ርብቃ ዌልች”

0
252

ታኅሳሥ 06/2016 ዓ.ም (አሚኮ) ዌልች ባለፈው ወር ማንቸስተር ዩናይትድ እና ፉልሃም ባደረጉት ጨዋታ አራተኛ ዳኛ ኾና ሠርታለች።በዚህም የመጀመሪያዋ ሴት አራተኛ ዳኛ ለመኾን በቅታለች፡፡

ከጊዜ ወደ ጊዜ ችሎታዋን ያጎለበተችው ዌልች፤ የእንግሊዝ እግር ኳስ የዳኞች ማኅበር በቀጣይ ሳምንት ፉልሃም እና በርንሌይን የሚያደርጉትን ጨዋታ በዋና ዳኝነት እንድትመራ መርጧታል ፡፡

ዳኛዋ በአውሮፓዊያኑ አቆጣጠር በ2022 የወንዶች ኤፍኤ ዋንጫ ጨዋታን በኮሚሽነርነት በመምራት በወንዶች እግር ኳስ በመሳተፍ ቀዳሚ እንስት ናት።

ስካይ ስፖርት እንደዘገበው ዌልች በ40 ዓመቷ ከባዱን እና በመላው ዓለም በርካታ ተመልካች ያለውን የእንግሊዝ ፕሪሚየር ሊግ ዋና ዳኛ የመኾን እድል አግኝታለች።

ርብቃ እግር ኳስን በዋና ዳኝነት እንድትመራ በመመረጧ በርካቶች ተደስተዋል፡፡በተለይ የእንግሊዝ ፕሪሚየር ሊግ የዳኞች አለቃ ሃዋርድ ዌብ ” ርብቃ ዌልች የፕሪሚየር ሊግ ዳኛ ኾና ስትሾም በማየቴ ተደስቻለሁ፤እሷ ጥሩ ችሎታ አላት፤ ላመነችበት ጉዳይ አታመነታም፡፡ ከመስመር እና ከአራተኛ ዳኞች ጋርም በንቃት ተናባ ትሠራለች፤ስለዚህ እድሉ ይገባታል” ብለዋል፡፡

በእንግሊዝ እግር ኳስ በተጫዋችነት ዝናና ክብርን የተጎናጸፈው ዋይኒ ሩኒም”እስካሁን ሴት ዳኛ የፕሪምየር ሊግ ጨዋታን ስትመራ አላየንም ነበር፡፡ አሁን የእሷ መምጣት ለእግር ኳሱ ውበትን ይጨምራል፤ሌሎች ሴቶችም ሙያውን እንዲቀላቀሉት አርዓያ ትኾናለች” ማለቱን ኢት ኔክስት የተሰኘ የመረጃ ምንጭ አስነብቧል።

ዳኛዋ ከዚህ በፊት በሕክምና ሳይንስ ዲግሪ ማግኘቷም ተገልጿል።

በሙሉጌታ ሙጨ

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here