ሌላው የሊግ ካፕ የፍጻሜ ተፋላሚ የሚለይበት ጨዋታ ዛሬ ይካሄዳል።

0
24
ባሕር ዳር፡ ጥር 27/2018 ዓ.ም (አሚኮ) በእንግሊዝ ሊግ ካፕ ማንቸስተር ሲቲ በሜዳው ኢትሃድ ከኒውካስል ዩናይትድ ጋር ምሽት 5:00 ይጫወታሉ።
ማንቸስተር ሲቲ በመጀመሪያው ዙር የግማሽ ፍጻሜ ጨዋታ ከሜዳው ውጭ ኒውካስልን 2ለ0 ማሸነፉ ይታወሳል።
በፕሪሚየር ሊጉም ከ24 ጨዋታዎች በ14ቱ አሸንፎ፣ በአምስቱ አቻ ተለያይቶ፣ በአምስቱ ተሸንፎ በ47 ነጥብ በሁለተኛነት መገኘቱ የቡድኑን ጥንካሬ ያመላክታል።
አሠልጣኝ ጋርዲዮላ “ዛሬ የምንጫወተው ለፍጻሜ በዌምብሌይ ስታዲየም ለመጫወት ነው” በማለት ለፍጻሜ እንደሚደርሱ አስረግጠው ተናግረዋል።
በጨዋታው ሳቪኒኾን፣ ጆን ስቶን፣ ጆስኮ ግቫርዲዮል፣ ሩብን ዲያስ እና ማቲዮ ኮቫቺች እንደማይሰለፉ ማንሲቲ ዶት ኮም አስነብቧል።
ተጋጣሚው የባለፈው ዓመት የሊግ ካፕ ዋንጫ አሸናፊ ኒውካስል ዩናይትድ በ2025/2026 የፕሪምየር ሊግ ውድድር ከ24 ጨዋታዎች ማሸነፍ የቻለው በዘጠኝ ጨዋታዎች ነው።
በስድስት ጨዋታዎች አቻ ተለያይቶ በዘጠኙ ደግሞ በመሸነፍ በ33 ነጥብ 11ኛ ነው።
የኒውካስል ዩናይትድ አሠልጣኝ ኤድ ሐው “ተጋጣሚያችን ፈታኝ ቡድን ነው፤ ዛሬ የምንጫወተው ግን ለማሸነፍ ነው” ብለዋል።
በኒውካስል ዩናይትድ በኩል ፋቢያን ሼር፣ ኢሚል ክራፍዝ እና ቲኖ ሊቨርሜንቶ በጉዳት ምክንያት እንደማይሰለፉ ታውቋል፡፡
ሁለቱ ቡድኖች በአራት የሊግ ካፕ ጨዋታዎች ተገናኝተው ሁለት – ሁለት ጊዜ አሸንፈዋል።
ይህም ሁለቱ ቡድኖች በሊግ ካፕ ጨዋታዎች ሲገናኙ ጠንካራ ፉክክር እንደሚያደርጉ ነው የሚያሳየው።
ዛሬ በድምር ውጤት የሚያሸንፈው ቡድን በቀጣይ በሚኖረው መርሐ ግብር ከአርሰናል ጋር በግዙፉ የዌምብሌይ ስታዲየም ለዋንጫ የሚጫወት ይኾናል።
በሙሉጌታ ሙጨ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here