“ኢትዮጵያ ብዙ የአፍሪካ ሀገራት ነጻነት እና ስታድየም ሳይኖራቸው የአፍሪካ ዋንጫን አስተናግዳለች” አቶ ኢሳያስ ጅራ

0
17

 

ባሕር ዳር: ጥር 26/2018 ዓ.ም (አሚኮ) የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ፕሬዝዳንት ኢሳያስ ጅራ ኢትዮጵያ የአፍሪካ ዋንጫን ለማስተናገድ ያላትን ፍላጎት ለካፍ ማቅረቧን ገልጸዋል።

የአፍሪካ ዋንጫን ለማዘጋጀት ስድስት ስታድየሞች እና 15 የመለማመጃ ሜዳዎች እንደሚያስፈልጉም ገልጸዋል።

ኢትዮጵያ የአፍሪካ ዋንጫን ለማስተናገድ እንደ ጥያቄ የሚነሱባትን ጉዳዮች መመለስ እንደሚገባት ተናግረዋል። ኢትዮጵያ እንግዶችን የማስተናገድ የቆዬ ልምድ እንዳላትም አንስተዋል። የስታድየም እና ሌሎች መሠረተ ልማቶችን ማጠናቀቅ እንደሚገባም ተናግረዋል።

የመንግሥት ቁርጠኝነት በዚሁ ከቀጠለ ሥራዎችን ማጠናቀቅ እንደሚቻልም ገልጸዋል። የአፍሪካ ዋንጫን ለማስተናገድ ውድድሩ ጠንከር ያለ እንደሚኾንም አንስተዋል። ካፍን የመሠረተች፣ የአፍሪካ ዋንጫን ያስጀመረች እና የአፍሪካ ዋንጫን ያዘጋጀችን ሀገር ፍላጎት ዝም ብሎ ማለፍ አይቻልም ነው ያሉት።

ኢትዮጵያ ብዙ የአፍሪካ ሀገራት ነጻነት እና ስታድየም ሳይኖራቸው የአፍሪካ ዋንጫን አስተናግዳለች ብለዋል።

ኢትዮጵያ የአፍሪካ ዋንጫን ማስተናገድ ይገባታል፤ የመንግሥት ፍላጎትም ከፍተኛ ነው፤ ካፍም በቂ ስታድየም ለሌላቸው ሀገራት ሰጥቶ በዚሁ አጋጣሚ ስታድየሞች እንዲገነቡ ማድረግ አለበት እንጂ ስታድየም ላላቸው ሀገራት ተደጋጋሚ መስጠት ትርጉም ያለው አይመስለኝም ነው ያሉት።

የአፍሪካ ዋንጫን እንድናዘጋጅ ዕድል መስጠት ስድስት ስታድየሞች እና 15 የመለማመጃ ሜዳዎች እንዲጠናቀቁ ዕድል መስጠት ነው ብለዋል።

የስፖርት መሠረተ ልማቶችን ከማሟላት ጎን ለጎን ጠንካራ ብሔራዊ ቡድን ለመገንባት ታዳጊዎች ላይ በትኩረት እየተሠራ መኾኑንም ተናግረዋል። በተሠራ ሥራም የኢትዮጵያ ከ17 ዓመት በታች ብሔራዊ ቡድን ከ22 ዓመታት በኋላ ለአፍሪካ ዋንጫ ማለፉን አንስተዋል። ታዳጊዎች ላይ ክለቦችም መሥራት እንደሚገባቸው ተናግረዋል።

ለታዳጊዎች በዕድሜ የሚገባቸውን ሥልጠና መስጠት፤ አመጋገባቸውን ማስተካከል እንደሚጠበቅም ገልጸዋል። ታዳጊዎችን እየመለመሉ መኾናቸውንም አስታውቀዋል። በታዳጊዎች ላይ የሚሠራው ሥራ ቀጣይነት እንደሚኖረውም ገልጸዋል። ሁሉም ታዳጊዎች ላይ መሥራት እንደሚገባውም አንስተዋል።

ለኢትዮጵያ ክብር የሚመጥን ብሔራዊ ቡድን መገንባት እንደሚያስፈልግም ተናግረዋል። በተሠራው ሥራ ተስፋ ታይቷል ይሄን ማጠናከር ያስፈልጋል ነው ያሉት። ከመሠረቱ ጀምሮ እንጂ በድንገት የሚገነባ ብሔራዊ ቡድን ሊኖር እንደማይችልም ገልጸዋል።

በሀገር ውስጥ ከሚሠራው ተግባር ባሻገር በውጭ የሚገኙ ትውልደ ኢትዮጵያውያንን መጠቀም እንደሚያስፈልግም ተናግረዋል። ጠንካራ እና ተፎካካሪ ለመኾን ከውስጥ እና ከውጭ ያለውን አቅም መጠቀም እንደሚጠበቅም ገልጸዋል። በቅንጅት መሥራት ከተቻለ ጠንካራ ብሔራዊ ቡድን መሥራት እንደሚቻልም ተናግረዋል።

የአፍሪካ ዋንጫን እንድናዘጋጅ ዕድሉ ከተሰጠን ጠንካራ ብሔራዊ ቡድን ይዘን መቅረብ አለብን፤ በራሳችን ድግስ የሌሎች ተመልካች መኾን የለብንምና ነው ያሉት።

ዘጋቢ:- ታርቆ ክንዴ

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here