የአፍሪካን ዋንጫ ያሳኩት የኮትዲቯር ተጫዋቾች ሽልማት ሊበረከትላቸው ነው።

0
307

ባሕር ዳር: የካቲት 06/2016 ዓ.ም (አሚኮ) በ34ኛው የአፍሪካ ዋንጫ አዘጋጇ ኮትዲቯር ናይጄሪያን 2ለ1 በመርታት ዋንጫ በመውሰዷ ለተጫዋቾች ገንዘብ፣ ዘመናዊ ቤት እና የኒሻን ሽልማት ከሀገሪቱ መንግሥት ሊበረከትላቸው ነው።

ለእያንዳንዱ ተጫዋችም 82 ሺህ ዶላር ቃል ተገብቶላቸዋል። ቪላ ቤትም እንደሚሸለሙ የሀገሪቱ ፕሬዚዳንት አስታውቀዋል።
ፕሬዚዳንት አላሳን ኦውታራ ተጫዋቾችን ” በእናንተ ትጋት ዓለም በጥሩ ነገር አውቆናል። የሀገሪቱ ገጽታም በበጎ ተገንብቷል፤ ሕዝቡንም አስደስታችሁታል እና ሽልማቱ አይበዛባችሁም ” ብለዋል።

የናይጄሪያ ብሔራዊ ቡድንም ሀገሩ ሲገባ ደማቅ አቀባበል እንደተደረገለት ዴይሊ ሜይል አስታውሷል።
ንሥሮቹ በዝሆኖቹ 2 ለ 1 በመሸነፋቸው በሚሊዮን የሚቆጠር ደጋፊዎቻቸውን ቢያሳዝኑም ጥረታቸው ግን በፕሬዚዳንት ቦላ ቲኒው ጥሩ ሽልማት አስገኝቶላቸዋል ነው የተባለው ።
ፕሬዚዳንቱ ለእያንዳንዱ የናይጄሪያ የእግር ኳስ ቡድን አባል የሀገሪቱን ከፍተኛ የክብር ኒሻን ሸልመዋል ።

ፕሬዚዳንት ቦላ ቲኒቡን ጠቅሶ ቢቢሲ እንደዘገበው በናይጀሪያ ዋና ከተማ አቡጃ አቅራቢያ ለሁሉም ተጫዋቾች አፓርታማ እና መሬት ተሰጥቷቸዋል።
በ34ኛው የአፍሪካ ዋንጫ ሦስተኛ ደረጃን ይዛ ያጠናቀቀችው ደቡብ አፍሪካም ለተጫዋቾች 52 ሺህ ዶላር ልትሰጣቸው መኾኑን የሀገሪቱን የብዙኃን መገናኛ ዋቢ አድርጎ ዴይሊ ሜይል ዘግቧል።

በ34ኛው አፍሪካ ዋንጫ አሸናፊ ኮትዲቯር 7 ሚሊዮን ዶላር ተሸልማለች። ሁለተኛዋ ናይጄሪያ 4 ሚሊዮን ዶላር፣ ደቡብ አፍሪካ እና ዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ እያንዳንዳቸው 2 ነጥብ 5 ሚሊዮን ዶላር እንካችሁ ተብለዋል።

በሩብ ፍጻሜው የተጫወቱት አራቱ ሀገራት እያንዳንዳቸው ደግሞ 1 ነጥብ 3 ሚሊዮን ዶላር ተሰጥቷቸዋል ተብሏል።
የዘንድሮው የአፍሪካ ዋንጫ በ67 ዓመታት ታሪኩ ከፍተኛ የተመልካች ቁጥር ተከታትሎታል። ሁለት ቢሊዮን የሚጠጋ ሕዝብ በዓለም ዙሪያ ተመልክቶታል።

በየጊዜው ለተጫዋቾች ቃል የሚገባው የሀገራት ሽልማት ተፈጻሚ ባለመኾኒ ብዙዎችን ማሳዘኑ የሚዘነጋ አይደለም። ለአብነትም እአአ በ1990 በዓለም ዋንጫ የሩብ ፍጻሜ እንግሊዝ እና ካሜሮን ተጫውተው የካሜሩን ቡድንም በወቅቱ ባሳየው ድንቅ ብቃቱ ዓለም አቀፍ አድናቆትን አትርፎ ነበር። የወቅቱ የሀገሪቱ መንግሥትም ለብሔራዊ ቡድኑ አባላት ዘመናዊ የመኖሪያ ቤት ለመሸለም ቃል ገብቶ ነበር።

ይሁንና ተጫዋቾች ሽልማታቸውን ሳይሰጣቸው ከ30 ዓመታት በላይ መጠበቃቸውን ቢቢሲ አስታውሷል። የጨዋታው አምበል የነበረው ተጫዋችም ሽልማቱን ሳይቀበል ከዚህ ዓለም በሞት ተለይቷል።

ዛሬ ላይ ግን ሽልማት በአብዛኛው እጅ በእጅ መኾኑ የአፍሪካ መንግሥታትን በጎነት ያሳያል እየተባለ ተብሏል።

በሙሉጌታ ሙጨ

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here