መድፈኞቹ የተሰጣቸውን ግምት መሸከም አቅቷቸው ይኾን?

0
84
ባሕር ዳር: ጥር 22/2018 ዓ.ም (አሚኮ) የሰሜን ለንደኑ ክለብ አርሰናል ዘንድሮ ለአራት የተለያዩ ዋንጫዎች ስኬት እንደሚጫወት ፍንጭ አሳይቷል፡፡
በአውሮፓ ሻምፒዮንስ ሊግ ካደረጋቸው ስምንት ጨዋታዎች ውስጥ ስምንቱንም ድል በማድረግ ወደ ጥሎ ማለፉ ተቀላቅሏል።
የእንግሊዝ ፕሪምዬር ሊግንም እስከ 23ኛ ሣምንት ድረስ በአራት ነጥቦች ልዩነት እየመራ ነው፡፡ በእንግሊዙ ካራባኦ ዋንጫም ለፍጻሜ ለመድረስ ከቼልሲ ጋር አንድ የመልስ ጨዋታ ብቻ ይቀረዋል፡፡ በእንግሊዝ ኤፍ ኤ ዋንጫም ወደ አራተኛው ዙር ለማለፍ ከዊጋን ጋር ጨዋታውን ያደርጋል፡፡
አርሰናል በ23ኛው ሳምንት የእንግሊዝ ፕሪምዬር ሊግ በሜዳው ከማንቸስተር ዩናይትድ ጋር ተጫውቶ የ2 ለ 3 ሽንፈት ስለገጠውም በስፋት መነጋገሪያ ኾኗል። መነጋገሪያ መኾኑም ብቻ ሳይኾን ተጨዋቾቹ ዋንጫ የማግኘት ተነሳሽነት ይጎላቸዋል የሚሉ ድምጾችም ጎልተው መሰማት ጀምረዋል፡፡
ባለፉት ሦስት ተከታታይ ዓመታት በእንግሊዝ ፕሪምዬር ሊግ ሁለተኛ ደረጃን ይዘው ያጠናቀቁት መድፈኞች 15 ጨዋታዎች በሚቀሩት የዘንድሮው የእንግሊዝ ፕሪምዬር ሊግ ከማንቸስተር ሲቲ እና ከአስቶንቪላ ጋር ያላቸው የነጥብ ልዩነት ወደ አራት በመጥበቡ ብዙ የክለቡ ደጋፊዎች ሥጋት ላይ መውደቃቸውን የስካይ ስፖርት መረጃ ይጠቁማል፡፡
ሚኬል አርቴታ በስድስት ዓመት አሠልጣኝነት ቆይታቸው በአርሰናል ቤት ጥሩ ነገሮችን እንደሠሩ ይነገራል። ትልቅ ዋንጫ የሌለበት ጥሩነት ግን ከዚህ በኋላ በአርሰናል ቤት ተቀባይነት እንደሌለው የሚገልጹ ድምጾችም በርካታ ናቸው፡፡
የቀድሞው የመድፈኞቹ አምበል ፈረንሳዊው ፓትሪክ ቪዬራ ከስካይ ስፖርት ጋር በነበረው ቆይታ መድፈኞቹ ወደ ሜዳ ሲገቡ በፍጹም ጥንካሬ እና ኀላፊነት በመውሰድ ጭምር መጫወት አለባቸው ብሏል፡፡ በእሱ ዕይታ መድፈኞቹ በጠንካራ ሥነ ልቦና ላይ አይገኙም፡፡
አርሰናል ከሊቨርፑል፣ ከኖቲንግሃም ፎረስት እና ከማንቸስተር ዩናይትድ ጋር ካደረጋቸው ሦስት ተከታታይ ጨዋታዎች ማሳካት የቻለው ሁለት ነጥቦችን ብቻ ነው፡፡
የአርሰናል የፊት መስመር ተጨዋቾች በድምሩ ካስቆጠሯቸው ግቦች በተሻለ የማንቸስተር ሲቲው አጥቂ ኧርሊንግ ሃላንድ ያስቆጠራቸው ግቦች መብለጣቸውም የመድፈኞቹን የፊት መስመር ተጨዋቾች በትችት እንዲብጠለጠሉ አድርጓቸዋል፡፡
የአርሰናሉ የመስመር አጥቂ ቡካዮ ሳካ በ13 ጨዋታዎች ላይ አንድም ግብ አለማስቆጠሩ እና ብዙ ተስፋ ተደርጎበት ከሊዝበን ወደ ለንደን የመጣው ቪክቶር ዮኬሬሽም በተጠበቀው ልክ አለመኾኑ ለመድፈኞቹ የሥጋት ምንጭ ኾነዋል፡፡
ለአርሰናል የዘንድሮ ዋንጫ ማጣት ሥጋት የኾኑት የፔፕ ጋርዲዮላዎቹ ማንቸስተር ሲቲዎች ቀጣይ ሁለት ጨዋታዎች ከቶተንሃም እና ከሊቨርፑል ጋር ከሜዳቸው ውጪ መኾኑ ለአርሰናል ደጋፊዎች የዋንጫ ተስፋን የሚፈነጥቁ ይመስላሉ፡፡
እ.አ.አ በ1980/81 የውድድር ዘመን የእንግሊዝ ፕሪምዬር ሊግን ያሳኩት አስቶንቪላዎች በስፔናዊው ኡናይ ኤምሬ እየተመሩ ከአርሰናል እና ከሲቲ ጋር የዋንጫ ተፎካካሪ የሚኾኑት እስከመቼ እንደኾነም አጓጊነቱ ቀጥሏል፡፡
በኦፕታ ግምት መሠረት አርሰናል አሁንም የእንግሊዝ ፕሪምዬር ሊግ ዋንጫን ለማሳካት የተሻለ (ከ81 በመቶ በላይ) ግምት ተሰጥቶታል፡፡
አሠልጣኝ ሚኬል አርቴታ ”በቀሪ ጨዋታዎች ሁሉ የመንፈስ ጥንካሬያችንን ልናሳይ ይገባል፤ በመልበሻ ቤት የምናሳየውን የማሸነፍ ሥነ ልቦና በሜዳ ውስጥም ልንደግመው ይገባል፤ በፍጥነት ወደ ቀደመ አቋማችን መመለስ እና ዕቅዳችንን ማሳካት ይኖርብናል” ብለዋል።
”ፍልሚያው ቀላል እንዳልኾነ ቀድመንም እናውቀዋለን፤ መውደቅ እና መነሳትም የእግር ኳስ ባህሪ ነው፤ እኛ ማድረግ ያለብን በቀጣይ ጨዋታ የኛን መልክ ይዘን መመለስ ብቻ ነው“ ያለው ደግሞ የአርሰናሉ የመስመር አጥቂ ቡካዮ ሳካ ነው፡፡
በተከታታይ ሦስት የእንግሊዝ ፕሪምዬር ሊግ ጨዋታዎች ነጥቦችን የጣሉት መድፈኞቹ በቀጣይ ቅዳሜ ከሜዳቸው ውጪ ከሊድስ ዩናይትድ ጋር በሚያደርጉት ጨዋታ የሚያስመለክቱን ነጥብም ከወዲሁ አጓጊ ኾኗል፡፡
ማንቸስተር ሲቲ ከሜዳው ውጪ ከቶተንሃም እና አስቶንቪላ በሜዳው ከብሬንትፎርድ የሚያደርጓቸው ጨዋታዎችም የተመልካቾችን ቀልብ እንደሚስቡ ይጠበቃል፡፡
ሦስቱ ስፔናዊያን አሠልጣኞች ሚኬል አርቴታ፣ ፔፕ ጋርዲዮላ እና ኡናይ ኤምሬ ለ2026 የእንግሊዝ ፕሪምዬር ሊግ ከፍተኛ ፉክክር ውስጥ ገብተዋል፤ ማን ይሳካለታል? ቀጣዮቹ 15 ጨዋታዎች ምላሽ ይኖራቸዋል፡፡
ዘጋቢ፡- እሱባለው ይርጋ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here