ባሕር ዳር፡ ጥር 22/2018ዓ.ም (አሚኮ) 35ኛውን የአፍሪካ ዋንጫ ሴኔጋል ሞሮኮን 1ለ0 አሸንፋ ሻምፒዮን መኾኗ ይታወሳል።
በዚህ የፍጻሜ ጨዋታ ላይ የሁለቱም ቡድን ተጫዋቾች እና ደጋፊዎች በፈጸሙት የስፖርታዊ ጨዋነት መጓደል ምክንያት ጨዋታው ለ17 ደቂቃ ያህል መቋረጡ አይዘነጋም።
ክስተቱም በዓለም አቀፍ ደረጃ ነቀፌታን ማስተናገዱ ይታወቃል።
ካፍም ጉዳዩን በሚገባ መርምሮ የሴኔጋል እና ሞሮኮ ብሔራዊ ቡድን አባላት እና ፌዴሬሽኖችን በገንዘብ እና ጥፋተኛ የተባሉ ተጫዋቾችን ብሎም አሠልጣኝ በጨዋታ እግድ መቅጣቱን አሚኮ ዲጂታል መዘገቡ ይታወሳል።
የካፍ ቅጣትን ተከትሎም የሞሮኮ እና ሴኔጋል የመገናኛ ተቋማት “ቅጣቱ የተጋነነ ነው። ጠንካራ ብሔራዊ ቡድኖችን ኾን ተብሎ ለማዳከም የተደረገ ሴራ ነው በተለይም በዓለም ዋንጫ ተሳትፏችን ላይ ከፍተኛ ኪሳራ ያስከትላል” ሲሉም ተቃውመውታል።
ካፍም የቅጣቱን ተፈጻሚነት በተመለከተ መግለጫ አውጥቷል።
የካፍ የዲሲፕሊን ኮሚቴ ባለሥልጣን እንዳብራሩት በሁለቱ ቡድኖች ላይ የተጣለው ቅጣት በአሜሪካ፣ ሜክሲኮ እና ካናዳ በሚዘጋጀው የዓለም ዋንጫ ጨዋታዎች ላይ አይተገበርም።
“በካፍ መርሐ ግብር በሚዘጋጁ የአህጉሩ ጨዋታዎች በተለይም በ2027ቱ የአፍሪካ ዋንጫ የማጣሪያ ጨዋታዎች ቅጣቱ ተፈጻሚ ይኾናል እንጅ ዓለም ዋንጫን አይመለከትም” በማለት አብራርቷል።
በሙሉጌታ ሙጨ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!



