በእግር ኳሱ ባለተሰጥኦ ታዳጊዎችን ለማፍራት ድጋፍ እና ክትትል እየተደረገ ነው፡፡

0
27
ደብረማርቆስ: ጥር 21/2018 ዓ.ም (አሚኮ) ከ13 እስከ 15 ዓመት በኾኑ ታዳጊዎች ተኪ ብሔራዊ ቡድን መገንባትን ዓላማ ያደረገ የታዳጊዎች የምልመላ ውድድር በአማራ ክልል ሲካሄድ መቆየቱ ይታወሳል፡፡
የደብረ ማርቆስ ከተማ አሥተዳደር ባዘጋጀው የውስጥ ውድድር ከሁለት ፕሮጀክቶች እና ከአንድ አካዳሚ የተመረጡ 15 ታዳጊ ተጫዋቾች በክልል ደረጃ በተካሄደው የምልመላ መስፈርት እንዲያልፉ ተደርጓል፡፡
ከእነዚህም ውስጥ ሁለት ተጫዋቾችን ማስመረጥ ሲቻል አንድ ተጫዋች ደግሞ በተጠባቂነት ማስመዝገብ ተችሏል፡፡
በብሔራዊ ቡድኑ ተመርጠው ሀገራቸውን እንዲያስጠሩ ማድረግን ዓላማ ባደረገው ውድድር ተሳትፈው ከተመረጡት ውስጥ ከአንተነህ እግር ኳስ አካዳሚ የተገኘው ሄኖክ ሰለሞን፣ ከብሩህ ተስፋ እግር ኳስ ፕሮጀክት ዳዊት መዝገቡ፣ ከሰውነት ደጉ የእግር ኳስ ፕሮጀክትን በተጠባባቂነት ትንሳኤ ደሳለኝ ነገን የተሻለ ለማድረግ እና በእግር ኳስ ራሳቸውን ከማሳየት አልፈው በብሔራዊ ቡድኑ ደረጃ ሀገራቸውን የመወከል ትልቅ ህልም ሰንቀው እየሠሩ መኾናቸውን ተናግረዋል፡፡
የትልልቅ ተጫዋቾችን አርዓያነት በመከተል ስኬታማ ለመኾን እንደሚጥሩ የተናገሩት ተጫዋቾቹ ታዳጊዎች ላይ በትኩረት ቢሠራ በእግር ኳሱ የተሻለ ውጤት ማምጣት እንደሚቻል ገልጸዋል።
የአንተነህ እግር ኳስ አካዳሚ አሠልጣኝ አንተነህ ያለው በበርካታ ፈተናዎች ውስጥ ታልፎ በክልል ደረጃ ተጫዋቾችን ማስመረጥ መቻሉ ለከተማ አሥተዳደሩ ትልቅ ዕድል መኾኑን ገልጸዋል። የእግር ኳስ ተሰጥኦ ያላቸውን ታዳጊዎች ይበልጥ የሚያበረታታ መኾኑንም ተናግረዋል፡፡
ተጫዋቾችን በሥነልቦና ከማዘጋጀት ጀምሮ የሚሰጣቸውን የቴክኒክ እና ታክቲክ ሥልጠናዎች በአግባቡ እንዲተገበሩ ጥረት መደረጉ ለውጤት አብቅቶናል ብለዋል። የታየውን ተስፋ ሰጭ ውጤትም በከተማ አሥተዳደሩ አጠናክሮ ማስቀጠል እንደሚገባም አስገንዝበዋል፡፡
እንደ ሀገር በእግር ኳስ ያጋጠመው ስብራት እንዲጠገን ካስፈለገ ታዳጊዎች ላይ የመሥራት ጉዳይ ከንግግር ያለፈ ተግባራዊ ርምጃዎች ሊታዩበት እንደሚገባም ተናግረዋል፡፡
የደብረ ማርቆስ ከተማ አሥተዳደር ባሕል፣ ቱሪዝም እና ስፖርት መምሪያ ኀላፊ ተስፋዬ አዕምሮ ተተኪ የእግር ኳስ ተጫዋቾችን ለማፍራት የሚደረገውን ጥረት ለማገዝ ስድስት ፕሮጀክቶች እና ሦሥት አካዳሚዎችን በማቋቋም እየተሠራ መኾኑን ገልጸዋል፡፡
ለ2028 ጠንካራ ብሔራዊ ቡድን ለመገንባት እየተደረገ ያለውን ሀገራዊ ተልዕኮ ለማሳካት ታዳጊዎች ላይ በትኩረት እየተሠራ ነው ያሉት ኀላፊው ታዳጊዎችን በአግባቡ በመመልመል፣ በሥልጠና እና ውድድር እንዲያልፉ በማድረግ በክልል ደረጃ ተጫዋቾችን ማስመረጥ መቻሉ አበረታች መኾኑን ተናግረዋል፡፡
በቀጣይም ባለተሰጥኦ ታዳጊዎችን ለማፍራት የሚደረገው ድጋፍ እና ክትትል ተጠናክሮ እንደሚቀጥልም አመላክተዋል።
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here