አዲስ አበባ: ጥር 20/2018 ዓ.ም (አሚኮ) ጅማ ዩኒቨርሲቲ ዓለም አቀፍ ውድድሮችን ማስተናገድ የሚችል መዋኛ ገንዳ ገንብቷል። መወኛ ገንዳው በአንድ ጊዜ ስምንት ተወዳዳሪዎችን ማስተናገድ የሚችል እና በኦሎምፒክ ስታንዳርድ 50 በ25 ቁመት እና ስፋት ያለው ነው።
ይህ መዋኛ ገንዳ በጅማ ዩኒቨርሲቲ እየተካሄደ የሚገኘውን የኢትዮጵያ ዩኒቨርሲቲዎች ስፖርት ፌስቲቫል እያስተናገደም ይገኛል።
መዋኛ ገንዳው ጅማ ዩኒቨርሲቲ የኢትዮጵያ ስፖርት ማዕከል ለመኾን ያስቀመጠውን ግብ የሚያግዝ መኾኑን ዩኒቨርሲቲው አስታውቋል።
የኢትዮጵያ ውኃ ስፖርቶች ፌዴሬሽን ጽሕፈት ቤት ኀላፊ ሽመልስ ደፋር ጅማ ዩኒቨርሲቲ ያስገነባው መዋኛ ገንዳ በፊና ስታንዳርድ የተገነባ ዓለም አቀፍ ውድድሮችን ማስተናገድ የሚችል መኾኑን ተናገረዋል።
በግምባታው ሂደት ፌዴሬሽኑ አስፈላጊውን ሙያዊ ድጋፍ እና ክትትል ማድረጉንም ገልጸዋል። እንደ ሀገር መሰል መዋኛ ገንዳዎች እንደሌሉ በማንሳትም ለውኃ ዋና ስፖርት ተጨማሪ አቅም እንደሚፈጥር ነው የገለጹት።
በጅማ ዩኒቨርሲቲ እየተካሄደ በሚገኘው የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች ስፖርት ፌስቲቫል የውኃ ዋና ውድድር በዛሬው ዕለት ተካሂዷል።
መዋኛ ገንዳው ደረጃውን የጠበቀ እና ምቹ መኾኑንም ተወዳዳሪ ዋናተኞች ተናግረዋል። ብቁ ስፖርተኞችን ለማፍራት ከውድድር ባለፈ ለልምምድ ክፍት መኾን እንዳለበት የጅማ ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች ተናግረዋል።
ዘጋቢ:- ባዘዘው መኮነን
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!



