ባሕር ዳር: ጥር 18/2018 ዓ.ም (አሚኮ) እንደ ኢትዮጵያዊቷ አበበች ጎበና፤ እንደ ኬኒያዊቷ የተፈጥሮ ሃብት ተሟጋች ዋንጋራ ማታይ ለሀገር እና ለወገን የሚተርፍ በጎ ሥራ ማከናወን ምንኛ መታደል ነው?
ለእንዲህ ዓይነቱ ዕድል ከበቁት ግለሰቦች አንዱ ናይጀሪያዊው ቪክቶር ጄምስ ኦሲምሄን ነው። እንደ አውሮፓ አቆጣጠር በ1998 በሌጎስ የተወለደ ቪክቶር ጄምስ ኦሲምሄን ከቤተሰቦቹ ሰባት ልጆች ውስጥ መቁረጫ ነው።
ከድሃ ቤተሰብ የተወለደው ኦሲምሄን በለጋ ዕድሜው የቤተሰቡን ሕይዎት ለማስቀጠል የግድ ሥራ ሠርቶ ገንዘብ ማግኘት ነበረበት። ከትምህርቱ ጎንም የቀን ሥራ እየሠራ ቤተሰቡን ይደግፋል።
በእንቅርት ላይ ጆሮ ገድፍእንዲሉ እናቱን በሞት ያጣው ብላቴና አባቱ የሚሠሩበት ተቋም ደግሞ እስከወዲያኛው ተዘጋ። የእነኦሲምሄን ቤተሰብም ክፉኛ ስቃይ ላይ ወደቀ።
ኦሲምሄንም የቤተሰቡን ሕይዎት ለመታደግ በሌጎስ ጎዳናዎች እየተዘዋወረ “ንጹሕ ውኃ” መሸጥ ጀመረ።
“ቆቅ” የኾነው ኦሲምሄን በኦሉሶሱን የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤት እየተማረ በትርፍ ጊዜው የገቢ ማስገኛ ሥራዎችን ይሠራል። ወዲህ ደግሞ እግር ኳስ በመጫወት ራሱን እያዝናና ነገን ይናፍቃል።
የኦሲምሄን የእግር ኳስ አጨዋወት አይተው ሳያጨበጭቡ የሚሄዱ አልነበሩም ማለት ይቻላል። በታዳጊው አጨዋወት የተደመመ አንድ ሰውም አይዞህ! በርትተህ ከሠራህ ነገ ጥሩ ደረጃ ትደርሳለህ በማለት የትጥቅ ድጋፍ አደረገለት።
ኦሲምሄን ጎዳና ላይ ሲጫወት “በርትተህ ከሠራህ ነገ ጥሩ ተጫዋች ትኾናለህ” ያሉትን ሰውየ ሃሳብ እያስታወሰ ጠንክሮ ሠራ። በአጨዋወት ክሂሉም በብዙዎች ዘንድ “ከዓይን ያውጣህ?” ተባለ።
በችሎታውም እንደ አውሮፖ አቆጣጠር በ2015 ሌጎስ በሚገኘው አልቲሜት ስትራይክስ አካዳሚን ተቀላቅሎ ስለ እግር ኳስ እየተማረ ተጫወተ። በናይጀሪያ ብሔራዊ ቡድንም ከ17 ዓመት በታች መመረጥ ቻለ። የሌሎችም የዓይን ማረፊያም ኾነ።
የጀርመኑን ቪኤፍኤል ወልፍስቡርግ ቡድን በደመወዝ እና በማትጊያ ጥቅማጥቅም ውል አስፈረመው።
ቪኤፍኤል ወልፍስቡርግ የተጀመረው የኦሲምሄን የፕሮፌሽናሊዝም እግር ተጫዋችነት በተለያዩ የአውሮፓ የእግር ኳስ ቡድኖችም እንዲፈለግ አደረገው። እንደ አውሮፓ አቆጣጠር በ2019 የፈረንሳዩ ሊል ቡድን በአምስት ዓመት ውል በ15 ሚሊዮን ዩሮ እና ጉርሻ አስፈረመው።
በ2020 ደግሞ የጣልያኑን ናፖሊ ቡድን በ80 ሚሊዮን ዩሮ ተቀላቀለ። ይህም በቡድኑ ታሪክ በጣም በውድ ዋጋ የተዘዋወረ ተጫዋች አድርጎታል። ቪክቶር ኦሲምሄን አሁን ለብሔራዊ ቡድኑ እንዲሁም በከፍተኛ ክፍያ ለተርክዬው ጋላታሳራይ ቡድን እየተጫወተ ይገኛል።
ይህ ድንቅ ተጫዋች ሃብቱን በአሸሼ ገዳሜ አያጠፋም። ገንዘቡን የቅንጦት ዕቃ በመግዛት አያባክንም። ለበጎ ሥራ ያውለዋል እንጅ።
በናይጀሪያ ሌጎስ ከተማ በቅርብ ርቀት በምትገኘው የኦሉሶሱን ከተማ ለሚገኙ የማኅበረሰብ አባላት የንጹሕ መጠጥ ውኃ አስቆፍሮ ተጠቃሚ አድርጓል። በሌጎስ እና በሌሎችም ከተሞች ዘመናዊ ትምህርት ቤቶችን በማስገንባት ትምህርት በነጻ እንዲሰጥ ለሕዝብ አስረክቧል።
አአካል ጉዳተኞችን በገንዘብ እና ዓይነት ይደግፋል። “ከሃብቴ 50 በመቶውን በመላው አፍሪካ የሚገኙ አካል ጉዳተኞችን ለመደገፍ ቃል እገባለሁ” ማለቱ ኒራልንድ በድረ ገጹ አስነብቧል።
ቪክቶር ኦሲምሄን ለካንሰር ህክምና የሚኾን ተቋም አሠርቶ ሥራ ላይ እንዲውል አድርጓል። አፍሪካውያን በታዳጊዎች የእግር ኳስ ልማት ላይ በመሥራት በርካታ ተጫዋቾችን በማፍራት ለዓለም እግር ኳስ ገበያ በማቅረብ ተጠቃሚ መኾን ይችላሉም ባይ ነው።
እርሱም በእግር ኳስ ልማት በመሠማራት በናይጀሪያ በተለያዩ አካባቢዎች የእግር ኳስ አካዳሚዎችን አስገንብቷል። በዚህም በርካታ ልጆች ሠልጥነው በታላላቅ ሊጎች እንዲመለመሉ እያደረገ ይገኛል።
የወደፊት ራዕዬ ናይጄሪያ ውስጥ ትልቅ የእግር ኳስ አካዳሚ መገንባት አፍሪካውያን ታዳጊዎች በአፍሪካውያን አሠልጣኞች እንዲሠለጥኑ በማድረግ አፍሪካን ተመራጭ ማድረግ ነው የሚለው በጎ አድራጊው ተጫዋች ትምህርት እና ጤና ላይም ከእስካሁኑ በበለጠ የመሥራት ዕቅድ አለው ሲል የዘገበው ዘ ኔሽን ኒውስ ፔፐር ነው።
አሁን ለናይጀሪያ ብሔራዊ ቡድን እና ለተርክዬው ጋላታሳራይ ቡድን የሚጫወተው ቪክቶር ኦሲምሄን አፍሪካውያን አዕምሯችንን ለበጎ ነገር ካዋልነው አፍሪካ ሰጭ እንጂ ተረጂ አትኾንም” ባይም ነው።
በሙሉጌታ ሙጨ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!



