10ኛው የኢትዮጵያ ዩኒቨርሲቲዎች ስፖርት ፌስቲቫል በጅማ ዩኒቨርሲቲ አስተናጋጅነት መካሄድ ጀምሯል።

0
72
አዲስ አበባ: ጥር 17/2018 ዓ.ም (አሚኮ)
ከጥር 17 እስከ የካቲት 1/2018 ዓ.ም በሚካሄደው የ2018 የኢትዮጵያ ዩኒቨርሲቲዎች ስፖርት ፌስቲቫል ከ49 ዩኒቨርሲቲዎች የተውጣጡ ከ7 ሺህ 500 በላይ ልዑካን ተሳታፊ ናቸው።
በመክፈቻ መርሐ ግብሩ የተገኙት በባሕልና ስፖርት ሚኒስቴር የስፖርት ዘርፍ ሚኒስትር ድኤታ መክዩ መሐመድ ስፖርት ከመዝናኛ እና ውድድር ባለፈ ለማኅበረሰብ እና ሀገር ግንባታ ያለው ሚና ከፍተኛ ነው ብለዋል።
እንደ ሀገር ስፖርትን ባሕሉ ያደረገ ማኅበረሰብ ለመፍጠር ትኩረት ተሰጥቶ እየተሠራ መኾኑንም ተናግረዋል።
በቅርቡ የተሻሻለው የስፖርት ፖሊሲም ይህን የሚያግዝ እና በስፖርቱ ዘርፍ ትልቅ ለውጥን የሚያመጣ መኾኑን ገልጸዋል።
ባለፉት ዓመታት መንግሥት የስፖርት ማዘውተሪያዎችን ከማስፋፋት በተጨማሪ የተጀመሩ ታላላቅ ስታዲየሞችን ለማጠናቀቅ በትኩረት እየሠራ ነውም ብለዋል።
ትምህርት ቤቶች የተወዳዳሪ እና ብቁ ስፖርተኞች መገኛ መኾናቸውንም አመላክተዋል። የኢትዮጵያ ዩኒቨርሲቲዎች ስፖርት ፌስቲቫል እና ውድድርም ተተኪ ስፖርተኞችን ለማግኘት ከፍተኛ ጠቀሜታ ያለው መኾኑን ተናግረዋል።
ሁሉም ዩኒቨርሲቲዎች ለውድድሩ ለሰጡት ትኩረት ምስጋና ያቀረቡት አቶ መክዩ ውድድሩ በስፖርታዊ ጨዋነት መርህ እና ኢትዮጵያዊነትን ባከበረ መልኩ እንዲካሄድም መልዕክት አስተላልፈዋል።
10ኛው የኢትዮጵያ ዩኒቨርሲቲዎች ስፖርት ፌስቲቫል ዛሬ በጅማ ዩኒቨርሲቲ አስተናጋጅነት ጅማሮውን ሲያደርግ በመክፈቻው በተካሄዱ የእግር ኳስ ጨዋታዎች አስተናጋጁ ጂማ ዩኒቨርሲቲ ኮተቤ ዩኒቨርሲቲን 5ለ0፣ አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ አዲስ አበባ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲን 1ለ0 አሸንፈዋል።
ዘጋቢ:- ባዝዘው መኮንን
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here