ሜዳው ላይ የፈሰሰው ልፋት በደስታ እንባ ተካሰ ለባለውለታው ቻሌ ሙሉጌታ የገንዘብ ድጋፍ ተደረገ።

0
58
ባሕር ዳር፡ ጥር 17/2018ዓ.ም (አሚኮ) ባለፈው ዓመት የአማራ ሚዲያ ኮርፖሬሽን የስፖርት ክፍል የባሕር ዳር ከተማ የስፖርት ሜዳዎችን ለ27 ዓመታት ያለመታከት በበጎ ፈቃደኝነት ሲንከባከብ የቆየውን የቻሌ ሙሉጌታን ታሪክ መዘገቡ ይታወሳል።
ዘገባውን ተከትሎ የብዙዎችን ቀልብ የሳበው የቻሌ አበርክቶ ዛሬ ፍሬ አፍርቶ ለባለውለታው የገንዘብ ድጋፍ ተበርክቶለታል።
የቻሌን የረጅም ዘመን ውለታ ለመካስ እና አሁን የሚገኝበትን ሁኔታ ለመደገፍ በኢንተርናሽናል አልቢትር ኃይለኢየሱስ ባዘዘው (ዶ.ር)፣ ዘመኑ ተሾመ (ዶ.ር) እና በዋርካው ተፈራ አማካኝነት የጥምር የባንክ አካውንት ተከፍቶ ከተለያዩ ደጋግ ግለሰቦች እና ተቋማት ገንዘብ ሲሠበሠብ ቆይቷል።
ትናንት ደግሞ የተሠበሠበው 87 ሺህ ብር ለባለውለታው ቻሌ ሙሉጌታ በይፋ ተሰጥቷል።
ገንዘቡን ያስረከቡት የባሕር ዳር ከተማ አሥተዳደር ባሕል ቱሪዝም መምሪያ ኀላፊ ጋሻው እንዳለው እና ኢንተርናሽናል አልቢትር ኃይለኢየሱስ ባዘዘው (ዶ.ር) ናቸው።
የአጼ ቴዎድሮስ ስታዲየምን ጨምሮ የከተማዋን የስፖርት ሜዳዎች በመንከባከብ “የሜዳዎች ባለውለታ” ተብሎ የሚታወቀው ቻሌ ሙሉጌታ የተደረገለትን ድጋፍ ሲረከብ ስሜቱን መቆጣጠር ተስኖት በደስታ እንባ ታጅቦ ምሥጋናውን አቅርቧል።
ዘጋቢ፦ መልሰው ጥበቡ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here