ዩኒቨርሲቲዎች የትውልድ መቅረጫ መሠረቶች ናቸው።

0
36
አዲስ አበባ: ጥር 17/2018 ዓ.ም (አሚኮ) የ2018 ዓ.ም የኢትዮጵያ ዩኒቨርስቲዎች ስፖርት ፌስቲቫል በጅማ ዩኒቨርሲቲ አስተናጋጅነት ዛሬ ይጀመራል።
በዚህ ውድድር ከ49 ዩኒቨርሲቲዎች የተውጣጡ ከ7 ሺህ 500 በላይ ስፖርተኞች በ15 የስፖርት አይነቶች ፉክክር ያደርጋሉ ተብሏል።
ውድድሩን በስኬት ለማስኬድ አስፈላጊው ቅድመ ዝግጅት መደረጉን የጅማ ዩኒቨርሲቲ ዛሬ በሰጠው መግለጫ አስታውቋል።
የዩኒቨርሲቲው ፕሬዝዳንት ጀማል አባፊጣ (ዶ.ር) ከጅማ ዞን ሕዝብ እና አሥተዳደር እንዲሁም ከኢትዮጵያ ዩኒቨርሲቲዎች ስፖርት ማኅበር ጋር በመተባበር ውድድሩን በውጤታማነት ለማስኬድ ቅድመ ዝግጅት አጠናቅቀናል ብለዋል።
“ዩኒቨርሲቲዎች የትውልድ መቅረጫ መሠረቶች ናቸው” ያሉት ፕሬዝዳንቱ በአካል እና በአዕምሮ የዳበረ ማኅበረሰብ ለመፍጠር ደግሞ ስፖርት አስፈላጊ መኾኑን አንስተዋል።
ተሳታፊዎች ለመጡበት ዩኒቨርሲቲ አምባሳደር በመኾን በስፖርታዊ ጨዋነት እና በኢትዮጵያዊነት ስሜት ውድድራቸውን እንዲያካሂዱም አሳስበዋል።
የኢትዮጵያ ዩኒቨርሲቲዎች ስፖርት ማኅበር ፕሬዝዳንት ዓባይ በላይሁን የዩኒቨርሲቲዎች ስፖርት ፌስቲቫል በ2008 ዓ.ም ከተቋረጠ በኋላ ባሳለፍነው ዓመት ቢመለስም በተሟላ ሁኔታ እንዳልተካሄደ አስታውሰዋል። ዘንድሮ በጥሩ ሁኔታ ይካሄዳልም ብለዋል።
አካዳሚክ ዕውቀትና ስፖርት አብሮ መሄድ እንዳለበት የተናገሩት አቶ አባይ እንደ ሀገር አሸናፊ ብሔራዊ ቡድን ለመገንባት የተያዘውን እቅድ ለማገዝ የዩንቨርስቲዎች ስፖርታዊ ውድድር አስፈላጊ ነው ብለዋል።
ዩኒቨርሲቲዎች ሰፊ የማኅበረሰብ ክፍል የሚገኝባቸው መኾናቸውን በመጥቀስም ይህ ፌስቲቫል ሀገራዊ ጉዳዮች የሚጎሉበት፣ አብሮነት እና አንድነት የሚጠናከርበት መኾኑንም አቶ ዓባይ በላይሁን ተናግረዋል። ተሳታፊዎችም ይህን ትልቅ አላማ ግብ እንዲያደርጉ አሳስበዋል።
የዩኒቨርሲቲዎች ስፖርታዊ ውድድር ተተኪ ስፖርተኞች የሚገኙበት መድረክ መኾኑን በማንሳትም ተቋማት እና ክለቦች አስፈላጊውን ምልመላ እንዲያደርጉም አቶ ዓባይ ገልጸዋል።
ውድድሩን በቴክኖሎጂ ለማገዝ እና ይበልጥ ስኬታማ ለማድረግም ሞባይል አፕ እና የውጤት መግለጫ ሲስተምን እና የመሳሰሉ ቴክኖሎጂዎች ተግባራዊ እንደሚደረጉ ተመላክቷል።
የውድድሩ መክፈቻ ዛሬ ከሰዓት በኋላ ይካሄዳል።
ዘጋቢ:- ባዘዘው መኮነን
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለ

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here