ባሕር ዳር: ጥር 17/2018 ዓ.ም (አሚኮ) በእንግሊዝ ፕሪምር ሊግ 23ኛ ሳምንት መርሐ ግብር ዛሬ አራት ጨዋታዎች ይደረጋሉ።
በተለይም አርሰናል መሪነቱን ለማስጠበቅ ማንቸስተር ዩናይትድ ደግሞ ደረጃውን ከፍ ለማድረግ የሚያደርጉት ጨዋታ በስፖርት ቤተሰቡ ዘንድ በጉጉት እየተጠበቀ ይገኛል።
ጨዋታው ምሽት 1:30 በአርሰናል ኤምሬትስ ይደረጋል።
አርሰናል በሊጉ ካደረጋቸው 22 ጨዋታዎች በ15ቱ አሸንፏል። በአምስት ጨዋታዎች አቻ ተለያይቶ፣ በሁለት ጨዋታዎች ተሸንፎ እና 50 ነጥብ በመያዝ ሊጉን እየመራ ይገኛል።
መድፈኞቹ ጨዋታውን አሸንፈው የዋንጫ ተገማችነታቸውን ይበልጥ ከፍ ለማድረግ ሰዓታትን እየጠበቁ ነው።
የአርቴታው ቡድን በሜዳው እንደመጫወቱ የማሸነፍ ቀድመ ግምቱ ከፍ ያለመሆኑን ዴይሊ ሜይል አስነበቧል።
በአንጻሩ ዩናይትድ የሊጉ ጉዞው ያዝ ለቀቅ ያለ እና የሚያስመዘግባቸው ውጤቶችም ቡድኑን ለግምት የማይመች ያደረጉ ናቸው። ሆኖም ባለፈው ሳምንት ማንቸስተር ሲቲን ያሸነፈበት መንገድ ዛሬስ በኤምሬትስ ምን ያሳያል ለሚለው ጥያቄ መልስ ፍለጋ የብዙዎችን ቀልብ አግኝቷል።
ሁለቱ ቡድኖች እንደ አውሮፓ አቆጣጠር ከ1995 ወዲህ በጠቅላላው በ74 ጨዋታዎች ተገናኝተዋል። ማንቸስተር ዩናይትድ 31 ጨዋታዎች በማሸነፍ የበላይነቱን ይዘዋል።
አርሰናል በ25 ጨዋታዎች ሲያሸንፍ በ18 ጨዋታዎች አቻ ተለያይተዋል።
ከ74ቱ ጨዋታዎች ውስጥ 37ቱን ጨዋታዎች በኢምሬትስ ስታዲየም ያደረጉ ሲኾን አርሰናል በ17ቱ ጨዋታዎች ድል በማድረግ የበላይነቱን ወስዷል።
ማንቸስተር ዩናይትድ ወደ አርሰናል ሜዳ አቅንቶ ያሸነፈው በ11 ጨዋታዎች ነው። በዘጠኝ ጨዋታዎች ደግሞ ነጥብ ተጋርተዋል።
ዛሬስ ማን ያሸንፍል?
የአርሰናል አሠልጣኝ ሚኬል አርቴታ የቡድኑ የፊት መስመር ተጫዋቾች በጥሩ ብቃት ላይ ይገኛሉ ነው ያሉት።
ከሁሉም የጨዋታ ክፍል በተለይ የአጥቂ ክፍል ተጫዋቾች በጥሩ አቋም ላይ መገኘታቸው ለቡድኑ ውጤት መሻት ወሳኝ ነው ብለዋል።
አሠልጣኝ አርቴታ ከማንቸስተር ዩናይትድ ከባድ ፈተና እንደሚጠብቃቸውም አልሸሸጉም። ይልቁንም “የሚገጥመንን ፈተና በድል ለመወጣት ተዘጋጅተናል” ነው ያሉት።
ፒዩሮ ሂንካፒዬ እና ሪካርዶ ካላፊዮሪ ከጉዳታቸው ሙሉ በሙሉ በማገገማቸው ይሰለፋሉ የሚሉ መረጃዎች እየወጡ ይገኛሉ።
የማንቸስተር ዩናይትድ ጊዜያዊ አሠልጣኝ ማይክል ካሪክ አርሰናል ጥሩ ቡድን ነው፤ እኛም ጥሩዎች ነን ብለዋል። ለማሸነፍ በቂ ዝግጅት አድርገናል ነው ያሉት። በዛሬው ጨዋታ ማዝራዊ ከአፍሪካ ዋንጫ መልስ ይሰለፋል ተብሏል።
ጨዋታው ወዲህ በኢትዮጵያውያን እግር ኳስ አፍቃሪያን ዘንድም በጉጉት የሚጠበቅ ነው። “የሰው ወርቅ አያደምቅ” ቢሆንም ቅሉ ወዲህ የማንቸስተር እና አርሰናል ደጋፊው ብዙ ነውና።
በሌሎች የዛሬ ቀን 11:00 መርሐ ግብሮች፦
ብሬንትፎርድ ከኖቲንግሃም ፎሬስት፣ ክሪስታል ፓላስ ከቸልሲ፣ ኒውካስትል ዩናይትድ ከአስቶን ቪላ ይጫወታሉ።
በሙሉጌታ ሙጨ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!



