ባሕር ዳር: ታኅሳሥ 5/2016 ዓ.ም (አሚኮ) በእንግሊዝ ፕሪሚየር ሊግ ዛሬ ኖቲንግሃም ፎሬስት እና ቶትንሐም ሆትስፐር ይጫወታሉ፡፡ በሊጉ ኖቲንግሃም 16 ጨዋታዎችን አድርጎ በስምንት ጨዋታዎች ተሸንፎ በሦስቱ ብቻ አሸንፏል፡፡ በ14 ነጥብም 16ኛ ደረጃ ላይ ይገኛል፡፡ በመኾኑም ይህን ጨዋታ ማሸነፍ ከወራጅ ቀጣናው በእጅጉ እንዲርቅ ያደርገዋል ሲል ኦፕታ አናሊስት በድረ ገጹ አስነብቧል፡፡
ቶትንሐም ሆትስፐር በ16 ጨዋታዎች ዘጠኝ ጨዋታዎች በማሸነፍ እና በአራቱ ተሸንፎ በ30 ነጥብ ደረጃው አምስተኛ ነው፡፡ ስለኾነም ቡድኑ ፎሬስትን ካሸነፈ ለዋንጫ ከሚፎካከሩት ቡድኖች ተርታ ያሰልፈዋል፡፡
ነገ ቅዳሜ ታኅሳሥ 6/2016 ዓ.ም ከሚደረጉ ጨዋታዎች መካከል ደግሞ የማንቸስተር ሲቲ እና የክሪስታል ፓላስ ግጥሚያ ተጠባቂ ኾኗል፡፡
ማንቸስተር ሲቲ ለበርካታ ዓመታት በእንግሊዝ ፕሪሚየር ሊግ የበላይ በመኾን የሦስትዮሽ ዋንጫዎችን ማንሳት ችሏል፡፡ በሊጉ በ16 ጨዋታዎች 33 ነጥብ በመሰብሰብ በደረጃ ሰንጠረዡ አራተኛ ደረጃ ላይ ተቀምጧል፡፡
በአንደኛ ደረጃ ላይ ከሚገኘው ሊቨርፑል በአራት ነጥብ ብቻ ርቋል። በእስካሁን ጨዋታውም 38 ግቦችን በማስቆጠር በፕሪሚየር ሊጉ “ምርጡ” ቡድን ለመኾን በቅቷል፡፡
የማንቸስተር ሲቲ እና የክሪስታል ፓላስ ጨዋታ በኢትሃድ ስታዲየም እንደመደረጉ ሲቲ አሸንፎ ወደ ሁለተኛ ደረጃ ከፍ ይላል የሚሉ የስፖርት ተንታኞች በርካታ ናቸው፡፡ ሲቲ በሜዳው ዘንድሮ ካደረጋቸው ሰባት የፕሪሚየር ሊግ ጨዋታዎች አምስቱን አሸንፎ በሁለቱ ጨዋታዎች አቻ መውጣቱን ልብ ይሏል፡፡
ክሪስታል ፓላስ በበኩሉ በፕሪሚየር ሊጉ 11ኛ ተከታታይ የውድድር ዘመን ላይ እየተጫወተ ነው፡፡ ምንም እንኳን ደረጃው ዝቅተኛ ቢኾንም፡፡
ክሪስታል ፓላስ በዚህ ዓመት በሊጉ ጥሩ አጀማመር ነበረው፤ ነገር ግን ባለፉት አምስት ጨዋታዎች ያገኘው አንድ ነጥብ ብቻ ነው፡፡ ደረጃውም 15ኛ ነው፡፡ ከወራጅ ቀጣናው በሰባት ነጥብ ብቻ ርቆ ይገኛል፡፡ ስለዚህ ይህን ጨዋታ ማሸነፍ ከቀይ መስመሩ በእጅጉ ለመራቅ ይጠቅመዋል፡፡
በሲቲ በኩል ኤርሊንግ ሀላንድ ምንም እንኳን ከእግር ጉዳቱ አገግሞ በጥሩ ኾኔታ ላይ ቢኾንም ለክሪስታል ፓላስ ጨዋታ ግን ዝግጁ ላይኾን ይችላል ሲል ፔፕ ጋርዲዮላን ጠቅሶ ዩሮስፖርት ዶት ኮም ፉት ቦል በድረ ገጹ ዘግቧል፡፡ በክሪስታል ፓላስ በኩል የክንፍ አጥቂው ዮርዳን አየው ቀይ ካርድ በማየቱ የአንድ ጨዋታ ቅጣት ስላለበት ተሰላፊ አይኾንም።
ግብ ጠባቂው ሳም ጆንስተን፣ የግራ መስመር ተከላካዩ ታይሪክ ሚቸል እና ዲን ሄንደርሰን ጉዳት ስላጋጠማቸው መሰለፋቸው አጠያያቂ ነው ተብሏል፡፡
ሁለቱ ቡድኖች በ33 ግጥሚያዎች ተገናኝተው ማንቸስተር ሲቲ በ21 ጨዋታዎች አሸንፏል፡፡ በስድስት ጨዋታዎች ደግሞ ተሸንፏል፤ በስድስት ጨዋታዎች ደግሞ አቻ ወጥቷል፡፡
በጨዋታው ማንቸስተር ሲቲ 73 በመቶ የማሸነፍ ቅድመ ግምት ተሰጥቶታል፡፡
በሌሎች ቅዳሜ ጨዋታዎች በርንማዉዝ ከሉተን ታዎን፣ ቸልሲ ከሸፊልድ ዩናይትድ፣ ኒውካስትል ዩናይትድ ከፉልሃም፣ በርንሌይ ከኤቨርተን ይጫወታሉ፡፡
እሑድ ደግሞ አርሰናል ከብራይተን፣ ብሬንትፎርድ ከአስቶን ቪላ፣ ዌስትሃም ዩናይትድ ከወልቭስ፣ ሊቨርፑል ከማንቸስተር ዩናይትድ የሚጫወቱ ይኾናል ሲል ቢቢሲ ስፖርት ዘግቧል፡፡
በሙሉጌታ ሙጨ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!