የምሥራቅ ጎጃም ዞን 23ኛው የባሕል ስፖርቶች ውድድር እና 19ኛው የባሕል ስፖርት ፌስቲቫል በደብረ ማርቆስ ከተማ መካሄድ ጀመረ።

0
47
ደብረ ማርቆስ፡ ጥር 14/2018 ዓ.ም (አሚኮ) የምሥራቅ ጎጃም ዞን 23ኛው የባሕል ስፖርቶች ውድድር እና 19ኛው የባሕል ስፖርት ፌስቲቫል ውድድር በዞኑ ባሕል፣ ቱሪዝም እና ስፖርት መምሪያ እንዲሁም በዞኑ ባሕል ስፖርቶች ፌዴሬሽን አዘጋጅነት እየተካሄደ ይገኛል፡፡
‎የምሥራቅ ጎጃም ዞን ባሕል፣ ቱሪዝም እና ስፖርት መምሪያ ኀላፊ ብርቄ ይዘንጋው ውድድሩ ባለፉት ሁለት ዓመታት በክልሉ ባጋጠመው የጸጥታ ችግር ምክንያት ተቀዛቅዞ የቆየውን የባሕል ስፖርት ለማነቃቃት የላቀ ፋይዳ ያለው መኾኑን ገልጸዋል፡፡
ውድድሩ የእርስ በእርስ ትውውቅ እና መስተጋብርን ከማጠናከር ባለፈ በክልል ደረጃ ለሚካሄደው የባሕል ስፖርቶች ውድድር እና ፌስቲቫል ዞኑን የሚወክሉ ተወዳዳሪዎችን ለመመልመል ታሳቢ ተደርጎ ስለመዘጋጀቱም አብራርተዋል፡፡
ስፖርት ሰላምን አጥብቆ ይፈልጋል ያሉት መምሪያ ኀላፊዋ የባሕል ስፖርቶችን ለማሳደግ እና ለማስፋት ኅብረተሰቡ በንቃት መሳተፍ ይጠበቅበታል ነው ያሉት፡፡
የምሥራቅ ጎጃም ዞን የባሕል ስፖርቶች ፌዴሬሽን ፕሬዝዳንት ሽታሁን ፀጋየ የባሕል ስፖርቶች የኅብረተሰቡን ባሕል፣ መተሳሰብ እና አብሮነት ለማጠናከር ያላቸውን ጉልህ አበርክቶ ከግምት ውስጥ በማስገባት በሰላም እጦት የተፈተነውን የባሕል ስፖርት ለማነቃቃት ትኩረት ተሰጥቶ እየተሠራ መኾኑን ተናግረዋል፡፡
የባሕል ስፖርቶች ለዘመናዊ ስፖርት ትልቅ መሠረት የጣሉ ናቸው ያሉት ፕሬዝዳንቱ ወጣቶች በመጤ ባሕሎች እንዳይጠለፉ እና የቆየውን ባሕል እና ወግ ጠብቀው ለትውል የማስተላለፍ አደራ እንዳለባቸው አስገንዝበዋል፡፡
የውድድሩ ተሳታፊዎች በበኩላቸው ላለፉት ሁለት ዓመታት ባጋጠመው የሰላም እጦት ምክንያት ተቋርጦ የቆየው ውድድር በመጀመሩ ደስተኛ መኾናቸውንም ተናግረዋል፡፡
ሰላም ለሁሉም ነገር መሠረት ነው ያሉት ተወዳዳሪዎች በስፖርታዊ ጨዋነት በውድድሩ በመሳተፍ በክልል ደረጃ በሚካሄደው የውድድር መድረክ የዞናቸውን ስም ለማስጠራት ዝግጅት ስለማድረጋቸውም ነው አስተያየታቸውን የሰጡት፡፡
‎ውድድሩ ከ13 ወረዳዎች እና ከከተማ አሥተዳደሮች የተውጣጡ ስፖርተኞች የሚሳተፉበት እንደኾነም ተገልጿል።
በስድስት የባሕል ስፖርት ዘርፎች ውድድሩ እንደሚካሄድም መምሪያው አስታውቋል፡፡
ይህ ዞን አቀፍ የባሕል ስፖርቶች ውድድር እና የባሕል ስፖርት ፌስቲባል ለተከታታይ ስምንት ቀናት የሚቆይ መኾኑም ተመላክቷል፡፡
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here