ባሕር ዳር: ጥር 13/2018 ዓ.ም (አሚኮ) 35ኛው የአፍሪካ ዋንጫ ከተጠናቀቀ ቀናቶች ተቆጥረዋል። በዚህ አህጉራዊ ውድድር ላይ የዓለምን ቀልብ የሳቡ ስፖርታዊ ትዕይንቶች እና ማራኪ ውድድሮች ተከናውነውበታል።
በአንጻሩ በአህጉራዊ ውድድሩ ከስፖርታዊ ጨዋነት ያፈነገጡ ባህሪያትም በጣት ከሚቆጠሩ ተወዳዳሪ ሀገራት ላይ ተስተውሏል። አህጉሪቱን ያስተቹ ከስፖርት ቤተሰቡ ያልተጠበቁ ተግባራትም የተስተዋሉበት ኾኖ አልፏል። ከነዚያም መካከል ለፍጻሜ የደረሱት ሴኔጋል እና ሞሮኮ ውድድር ላይ የተስተዋለው ያልተገባ ክስተት ለትችት የዳረገ ነበር።
ምንስ ዳኛ ቢሳሳት አንድ ሀገሩን ወክሎ የመጣ ብሔራዊ ቡድን ከሜዳ አቋርጦ ይወጣል ወይ ያስባለውን ትችት የሴኔጋል ተጨዋቾች በተግባር አድርገውታል። የዓለም የስፖርት ቤተሰቡ ትችት እና የካፍ ውሳኔም ገና እየተጠበቀ ይገኛል።
በዚሁ የ35ኛው የአፍሪካ ውድድር ላይ ያልተገባ ባህሪ ካሳዩት ውስጥ በአልጀሪያ እና በናይጀሪያ መካከል በተካሄደው ጨዋታ ላይ የተከሰተው ትዕይንትም ይገኝበታል።
በዚህም ምክንያት የአፍሪካ እግር ኳስ ኮንፌዴሬሽን (ካፍ) በአልጄሪያ ላይ የ100 ሺህ አሜሪካን ዶላር ቅጣት አስተላልፏል።
ቅጣቱ የተላለፈው አልጄሪያ እና ናይጄሪያ ባደረጉት የአፍሪካ ዋንጫ የሩብ ፍፃሜ ጨዋታ ላይ የአልጀሪያ ብሔራዊ ቡድን ሁለት ተጨዋቾችና ደጋፊዎቻቸው ተገቢነት የሌለውን ባሕሪ በማሳየታቸው እንደሆነ ተገልጿል።
በዚህም ግብ ጠባቂው ሉካ ዚዳን ሁለት ጨዋታዎችን ሲታገድ ተከላካዩ ራፊክ ቤልጋሊ ከአራት ጨዋታዎች እንዲታገድ ተወስኖበታል።
ቅጣቶቹ በፈረንጆቹ 2027 የአፍሪካ ዋንጫ የማጣሪያ ጨዋታዎች ወቅት ተግባራዊ እንደሚገደረግም ተመላክቷል።
በተጨማሪም ደጋፊዎች ተቀጣጣይ ነገሮችን በመጠቀም፣ ቁሳቁስ በመወርወር እና የዳኝነት ቡድኑ ላይ የጥቃት ምልክቶች በማሳየታቸው ምክንያት በአልጄሪያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ላይ የገንዘብ ቅጣቱ ተጥሏል።
የአልጄሪያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ውሳኔውን በመቃወም የይግባኝ ሂደት መጀመሩንና በህጋዊ መንገዶች እንደሚከላከል ማሳወቁን ፉትቦል ዋን ዘግቧል።
በሰለሞን አንዳርጌ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!



