የፍጻሜ ጨዋታው ግርግር እና የሚጠበቀው የካፍ እርምጃ።

0
60

 

ባሕር ዳር: ጥር 11/2018 ዓ.ም (አሚኮ) በ35ኛው የአፍሪካ ዋንጫ ሴኔጋል አስተናጋጇን ሞሮኮ 1ለዐ አሸንፋ ሻምፒዮን መኾኗ ይታዎቃል።

የፍጻሜው ጨዋታም የተለያዩ አወዛጋቢ ክስተቶች አስተናግዶ ነው ያለፈው።

የመጀመሪያው አወዛጋቢ ክስተት “ሴኔጋል ያስቆጠርኩት ግብ የተሻረው በስህተት ነው” በሚል ከዳኛ ጋር የተፈጠረ እሰጥ አገባ ነበር።

ይህ በዚህ እንዳለ ጨዋታው ባዶ ለባዶ ተጠናቀቀ ሲባል 98ኛው ደቂቃ የሴኔጋል ተጫዋች በሞሮኮው ተጫዋች ላይ ጥፋት ሠርቷል የሚል ቅሬታ ቀረበ።

ጉዳዩም ወደ ቫር ውሳኔ አመራ። በቫር ውሳኔ መሠረትም ሞሮኮ የፍጹም ቅጣት ምት ተሰጣት።

የሴኔጋል አሠልጣኝ ውሳኔውን በጽኑ ከመቃወም እና የክስ ‘ሪዘርቭ’ ከማስመዝገብ ባለፈ ተጫዋቾች ጨዋታውን አቋርጠው እንዲወጡ አደረጉ። ተጫዋቾችም ወደ መልበሻ ክፍል ተመለሱ። ጨዋታው ለ17 ደቂቃ ያህልም ተቋረጠ።

ጨዋታውን በቀጥታ ሲከታተሉ የነበሩ 79ሺህ 500 ተመልካቾች እና ጨዋታውን በተለያዩ የመገናኛ አውታሮች ሲከታተሉ የነበሩ ጨዋ የስፖርት ቤተሰቦች ኹሉ በሁኔታው አንገታቸው ደፉ።

የኋላ ኋላ ጨዋታው በገላጋዮች እና በሴኔጋሉ ሁነኛ አጥቂ በሳዲዮ ማኔ ትጋት የሴኔጋል ተጫዋቾች ወደ ሜዳ ተመልሰው ለ17 ደቂቃ ያህል የተቋረጠው ጨዋታ ቀጥሎ ፍጹም ቅጣት ምቱን የሞሮኮው ብራሂም ዲያዝ ቢመታም ወደ ግብነት ግን መቀየር አልቻለም።

ጨዋታው ወደ ተጨማሪ ሰዓት አምርቶ የሴኔጋሉ ፓፔ ጉዬ ባስቆጠራት ግብ ሞሮኮ ተሸነፈች። ሴኔጋልም አሸንፋ ሻምፒዮን ኾነች።

ጨዋታውን በቀጥታ በስታዲየም ተገኝተው የተከታተሉት የፊፋው ፕሬዝዳንት ያዩትን ነገር ማመን እንዳቃታቸው አልሸሸጉም።

የአፍሪካ እግር ኳስ ኮንፌዴሬሽን (ካፍ)ም ዛሬ በጉዳዩ ዙሪያ መግለጫ አውጥቷል።

የካፍ ፕሬዝዳንት ፓትሪስ ሞሴፔ(ዶ.ር) የሴኔጋል ብሔራዊ ቡድን ተጨዋቾች ያሳዩት ድርጊት ተገቢ አይደለም። ግን ደግሞ አፍሪካውያንን አይወክልም ብለዋል።

የፊፋ ፕሬዝዳንት ጂያኒ ኢንፋንቲኖም በአፍሪካ ዋንጫ የፍፃሜ ጨዋታ ላይ የተከናወኑ ድርጊቶችን በፅኑ አውግዘው በአጥፊዎች ላይ ርምጃ እንዲወሰድ አሳስበዋል።

ካፍ እና መላው ቀናኢ የስፖርት ቤተሰቦችን በተለይም አፍሪካውያን በድርጊቱ በእጅጉ ማዘናቸውን የካፍ ፕሬዝዳንት ጠቁመዋል።

ካፍ ጉዳዩን መረጃ እና ማስረጃን መሠረት በማድረግም በአጥፊዎች ላይ አስተማሪ እና የማያዳግም ርምጃ ለመውሰድ ተዘጋጅቷል ሲሉ ፕሬዝዳንት ፓትሪስ ሞሴፔ (ዶ.ር) ተናግረዋል።

በሙሉጌታ ሙጨ

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here