ሞሮኮ የደገሰችውን ራሷ ትበላው ይኾን?

0
80
ባሕር ዳር፡ ጥር 10/2018 ዓ.ም (አሚኮ) ሞሮኮ የደገሰችው 35ኛው የአፍሪካ ዋንጫ 24 ሀገራትን አሳትፎ ዛሬ ፍጻሜውን ያገኛል። ደጋሿ ሞሮኮ እና ምዕራባዊቷ ሴኔጋል በሚያድርጉት የዋንጫ ጨዋታ ነው የሚቋጨው።
ጨዋታው ምሽት 4:00 ሰዓት ራባት ከተማ በሚገኘው እና 68 ሺህ 700 ተመልካች በሚይዘው ዘመናዊው የንጉሥ ሙላይ አብደላህ ስታዲየም ይካሄዳል። ሁለቱ ቡድኖች እንደ አውሮፓውያኑ አቆጣጠር ከ2007 ወዲህ በስድስት ጨዋታዎች ተገናኝተው ሞሮኮ በአራቱ በማሸነፍ የበላይነቱን ይዛለች፡፡
ሴኔጋል በአንድ ጨዋታ ብቻ ነው ያሸነፈችው፡፡ በአንድ ጨዋታ ደግሞ አቻ ተለያይተዋል፡፡
የሞሮኮ ብሔራዊ ቡድን ጠንከራ የተከላካይ ክፍል መገንባቱ ይነገራል፡፡ መገለጫው ደግሞ በዚህ የአፍሪካ ዋንጫ ከስድስት ጨዋታዎች አንድ ግብ ብቻ ማስተናገዱ ነው፡፡
ቡድኑ እንደ አሽራፍ ሐኪሚ እና ብራሂም ዲያዝ የመሳሰሉ ብቃት ያላቸውን ፕሮፌሽናል ተጫዋቾችን ይዟል፡፡
በአትላስ አናብስት (ሞሮኮ) በኩል ከቁልፍ ተጫዋቾች መካከል በዛሬው ጨዋታ የማይሰለፈው አዘዲን ኦናሂን ብቻ መኾኑ ታውቋል፡፡
የሞሮኮ ብሔራዊ ቡድኑ አሠልጣኝ ዋሊድ ሬግራጉይ ሴኔጋል ጥሩ አሠልጣኝ እና ጥሩ ቡድን አላት ነው ያሉት፡፡ “እኛም ጠንካራ ቡድን አለን፤ በሜዳችን እና በደጋፊዎቻችን ፊት እንደመጫዋታችን ከእነርሱ የበለጠ አቅም በመፍጠር አሸንፈን መላውን የሞሮኮ ሕዝብ ለማስደሰት እንጫወታለን” ብለዋል አሠልጣኙ።
የሴኔጋል አሠልጣኝ ፓፔ ቲያው በበኩላቸው ከአስተናጋጅ ሀገር ጋር መጫወት ቀላል ባይኾንም ቡድናቸው ዋንጫውን ለመውሰድ በቴክኒክ፣ በታክቲክ እና በሥነ ልቦና መዘጋጀቱን ተናግረዋል፡፡
የቴራንጋ አናብስት (ሴኔጋል) የፊት መስመር በሳዲዮ ማኔ እንደሚመራም ነው አሠልጣኙ የጠቆሙት፡፡
በዚህ ወሳኝ ጨዋታ ተከላካዩ ካሊዱ ኩሊባሊ እና ሃቢብ ዲያራ በቅጣት የማይሰለፉ ተጫዋቾች ናቸው፡፡
ምሽት 4:00 ሰዓት በሚደረገው ጨዋታ ሞሮኮ የራሷን ድግሥ ራሷ ትበላው ይኾን? ወይስ ለሴኔጋል አሰልፋ ትሰጣለች? ምሽት ምላሹን እናየዋለን።
በሙሉጌታ ሙጨ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here