ባሕር ዳር: ጥር 06/2018 ዓ.ም (አሚኮ) 35ኛው የአፍሪካ ዋንጫ ዛሬ ሁለት የግማሽ ፍጻሜ ጨዋታዎችን ያስተናግዳል።
ምሽት 2:00 ምዕራብ አፍሪካዊቷ ሴኔጋል ከሰሜን አፍሪካዊቷ ግብጽ ይጫወታሉ።
ሴኔጋል እንደ አውሮፖ አቆጣጠር በ2021 ካሜሩን ያዘጋጀችውን የአፍሪካ ዋንጫ መውሰዷ ይታወሳል።
በ35ኛው የአፍሪካ ዋንጫ ምድብ አራት ላይ የተደለደለችው ሴኔጋል ካደረገቻቸው ሦሥት ጨዋታዎች ሁለቱን አሸንፋ በአንዱ አቻ በመለያየት በሩብ ፍጻሜ ጨዋታ ማሊን 1ለ0 በመርታት ነው ለግማሽ ፍጻሜ የደረሰችው።
የሴኔጋል ቡድን በሳዑዲው አል ናስር በሚጫወተው ሳዲዮ ማኔ ፊት አውራሪነት የሚመራ ቢኾንም ሁሉም ቋሚ ተሰላፊዎች ፕሮፌሽናል ናቸው።
የሴኔጋል ዋና አሠልጣኝ ፓፔ ቲያው የግብጽ ቡድን በአፍሪካ ውስጥ እጅግ ከዋከብት ተጫዋቾችን የያዘ ነው ብለዋል።
አሠልጣኙ አክለውም ቡድኑ በታክቲካል ዲሲፕሊን የተካነ እና ልምድ ያለው ነው። ነገር ግን እኛም ለማሸነፍ ቆርጠን ተነስተናል ነው ያሉት።
ተጋጣሚዋ ግብጽ ምድብ ሁለት ካደረገቻቸው ሦሥት ጨዋታዎች ሁለቱን በማሸነፍ እና በአንዱ አቻ ተለያይታ ነው ለሩብ ፍጻሜ የደረሰችው።
በሩብ ፍጻሜ ጨዋታ ኮትዲቫርን 3ለ2 አሸንፋ ነው ግማሽ ፍጻሜውን የተቀላቀለችው።
የግብጽ ዋና አሠልጣኝ ሆሳም ሀሰን ሴኔጋል እንደነ ሳዲዮ ማኔ ያሉ ብቃት ያላቸው ተጫዋቾች ባለቤት በመኾናቸው ብናከብራቸውም እኛ ግን ሰባት ጊዜ የአፍሪካ ሻምፒዮን በመኾን የተለየን ያደርገናል ነው ያሉት።
“ዛሬ የምንጫወተው የአፍሪካን ዋንጫ ለስምንተኛ ጊዜ ለማንሳት እያለምን ነውና እናሸንፋለን “ብለዋል።
በሙሉጌታ ሙጨ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!



