ባሕር ዳር: ጥር 03/2018 ዓ.ም (አሚኮ) በጣሊያን ሴሪኤ 19ኛ ሳምንት መርሐ ግብር ዛሬ ቀን 11:00 ላይ ፊዮሪንቲና እና ኤሲ ሚላን የሚያደርጉት ጨዋታ ተጠባቂ ነው።
ኤሲ ሚላን በሴሪኤው ካደረጋቸው 18 ጨዋታዎች 39 ነጥብ በመያዝ በሁለተኛነት ተቀምጧል። ቡድኑ የዛሬውን ጨዋታ ካሸነፈ ነጥቡን 42 በማድረስ መሪ የመኾን ዕድሉን ያሰፋለታል።
ፊዮሪንቲና ደግሞ በደረጃ ሰንጠረዡ 13 ነጥብ ብቻ በመያዝ ወራጅ ቀጣናው ውስጥ 17ኛ ላይ ይገኛል። በመኾኑም ጨዋታውን ካሸነፈ ከወራጅ ቀጣናው መውጣት ያስችለዋል።
የሁለቱ ቡድኖች ጨዋታ መሪ ለመኾን በሚያልም እና ከወራጅ ቀጣና ለመውጣት በሚታትር ቡድኖች መካከል በመኾኑ ከፍተኛ ፉክክር ይደረግበታል ተብሎ ተጠብቋል።
ሌላው የሴሪኤ አጓጊ ጨዋታ በኢንተር ሚላን እና ናፖሊ መካከል የሚደረገው ነው። ኢንተር ሚላን ካደረጋቸው 18 ጨዋታዎች 42 ነጥብ በመሠብሠብ የሴሪኤው መሪ ነው። ጨዋታውን ካሸነፈ መሪነቱን ይበልጥ የሚያጠናክርበት ይኾናል።
ተጋጣሚው ናፖሊ ደግሞ በ38 ነጥብ አራተኛ ደረጃ ላይ ይገኛል። ጨዋታውን ማሸነፍ ደረጃውን ወደ ሁለተኛነት ማሳደግ ያስችለዋል።
ሁለቱ ቡድኖች ካላቸው ወቅታዊ አቋም እና ነጥብ ከመሻት አኳያ ማራኪ ጨዋታ እና ብርቱ ፉክክር እንደሚያደርጉ ተጠብቋል። ሴሪኤውን ኢንተር ሚላን በአንደኛነት በመምራት ላይ ይገኛል።
ኤሲ ሚላን በሁለተኛ እና ሮማ በሶስተኛ ደረጃን ይዘው ይገኛሉ ሲል ያስነበበው ቢቢሲ ነው።
በሙሉጌታ ሙጨ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!



