አጓጊው የሪያል ማድሪድ እና የባርሴሎና ጨዋታ

0
14
ባሕር ዳር: ጥር 03/2018 ዓ.ም (አሚኮ) የስፔን ሱፐር ካፕ ጨዋታ ከቅርብ ዓመታት ወዲህ በአራት ቡድኖች መካከል ጠንካራ እና ተጠባቂ ፉክክር የሚደረግበት መርሐ ግብር ነው።
ዘንድሮም ባርሴሎና፣ አትሌቲክ ቢልባኦ፣ ሪያል ማድሪድ እና አትሌቲኮ ማድሪድ እየተሳተፉበት ይገኛሉ።
በተለይ የምንጊዜም ተቀናቃኝ የኾኑት ሪያል ማድሪድ እና ባርሴሎና የሚያደርጉት ጨዋታ ትርጉሙ ከስፖርታዊ ጨዋታ ባሻገር ፖለቲካዊ አንድምታም እንዳለው ይነገራል።
በመኾኑም ጨዋታው ከስፔናውያን ባለፈ ስፓኒሽ ቋንቋ በሚናገሩ የሌሎች ሀገራት ዜጎች እንዲሁም በስፖርት ቤተሰቡ ዘንድ በጉጉት የሚጠበቅ ጨዋታ ነው።
ባርሴሎና አትሌቲክ ቢልባኦን 5 ለ 0 እንዲሁም ሪያል ማድሪድ አትሌቲኮ ማድሪድ 2 ለ 1 በማሸነፍ ዛሬ ለሚካሄደው ተጠባቂ የኤል ክላሲኮ የፍጻሜ ጨዋታ ተገናኝተዋል።
ጨዋታው ምሽት 4 ሰዓት በሳዑዲ አረቢያ 62 ሺህ 345 ተመልካች በሚይዘው ንጉሥ አብደላ ስፖርት ስታዲየም ይካሄዳል። ዐይኖች ሁሉ ትኩረታቸው በዚህ ጨዋታ ላይ ይኾናል እየተባለም በመሞካሸት ላይ ነው።
ሪያል ማድሪድ እና ባርሴሎና በታሪክ በተገናኙባቸው 262 ጨዋታዎች ሪያል ማድሪድ በ106 ጨዋታዎች በማሸነፍ እና 445 ግቦችን ባርሴሎና መረብ ላይ አስቆጥሯል።
ባርሴሎና ደግሞ በ104 ጨዋታዎችን አሸንፏል፤ 433 ግብም አስቆጥሯል። ሁለቱ ቡድኖች በ52 ጨዋታዎች ደግም አቻ ተለያይተዋል ሲሉ ላሊጋ ኦፊሻል እና ስፖርት ሞል አስነብበዋል።
👉 ዛሬስ?
ምሽት 4 ሰዓት ሳዑዲ አረቢያ በሚገኘው ግዙፉና ቅንጡ በኾነው ንጉሥ አብደላ ስፖርት ስታዲየም የሚደረገው ጨዋታ ምላሹን ይሰጠናል።
በባርሴሎና በኩል የመሰለፉ ነገር አጠራጣሪ የነበረው ላሚን ያማል ይጫወታል ተብሏል። በሪያል ማድሪድም አንቶኒዮ ሩዲገር እና ራውል አሴንሲዮ በጨዋታው እንደሚሰለፉ ተዘግቧል።
በሙሉጌታ ሙጨ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here