ጥፋት የፈጸሙ ተጫዋቾችን ለ10 ደቂቃ ከሜዳ የሚያርቀው ሰማያዊ ካርድ ሥራ ላይ ሊውል ነው።

0
293

ባሕር ዳር: የካቲት 01/2016 ዓ.ም (አሚኮ)ጥፋት የፈጸሙ ተጨዋቾችን ለ10 ደቂቃ ከሜዳ የሚያርቀው ሰማያዊ ካርድ ሥራ ላይ ሊውል ነው።

የቢጫ እና የቀይ ካርዶች በእግርኳስ ለመጀመሪያ ጊዜ በ1970 እኤአ በተካሄደው የሜክሲኮ የዓለም ዋንጫ ተግባራዊ ከተደረገ በኃላ የመጣ ተጨማሪ ካርድ ነው ሰማያዊ ካርድ ብሏል የቴሌግራፍ ዘገባ።

የእግር ኳስ ሕጎችን የሚያወጣው የዓለም አቀፍ እግር ኳስ ማኅበራት ቦርድ (አይኤፍኤቢ) ከቢጫና ቀይ ካርድ በተጨማሪ ሰማያዊ ካርድ ሥራ ላይ ሊያውል መኾኑ ተሰምቷል።

ሰማያዊ ካርድ ሆን ብለው ጥፋት ለሚፈጽሙ ተጫዋቾች እንዲሁም በጨዋታው ዳኛ ውሳኔዎች ላይ ያልተገባ ምላሽ ለሚያሳዩ ተጫዋቾች ይሰጣል ተብሏል። በቅጣቱም አጥፊ ተጨዋች ለአስር ደቂቃዎች ያህል ከጨዋታ ሜዳ ውጭ እንዲቆዩ ያደርጋል።

ሕጉ ተጫዋቾች ለአስር ደቂቃዎች ከጨዋታ ውጭ ከቆዩ በኋላ ተመልሰው ወደ ሜዳ ገብተው ጨዋታውን እንዲቀጥሉም ይፈቅዳል። ዘ ቴሌግራፍ እንደዘገበው ሰማያዊ ካርድ በተወሰኑ የእንግሊዝ ኤፍ ኤ ካፕ ውድድሮች ላይ እንደሚሞከርም ነው የተገለጸው።

ሰማያዊ ካርዱ ከቢጫ ካርድ ጋር ተመሳሳይ ውጤት እንዳለው የተገለጸ ሲሆን በዚህም አንድ ተጫዋች በጨዋታ ላይ ሁለት ሰማያዊ ካርድ ካዬ ልክ እንደ ሁለት ቢጫ ካርድ ተቆጥሮ ከሜዳ ይባረራል። ከዚህ በተጨማሪም አንድ ሰማያዊ እና አንድ ቢጫ ካርድ ያዬ ተጫዋችም በቀይ ካርድ ከጨዋታ ሜዳ ይሰናበታል።

አዲሱ ሕግ ታች ባሉ አማተር የእግር ኳስ ውድድሮች ላይ ተሞክሮ ተጫዋቾች የሚፈጽሙትን ጥፋት 38 በመቶ እንዲቀንስ ማድረጉም ተዘግቧል።ይሁንና ፊፋን ጨምሮ ከበርካታ የእግር ኳስ ማኅበረሰብ ዘንድ ከወዲሁ ተቃውሞ እየደረሰበት መኾኑን ዘገባዎች ያመለክታሉ።

ዘ ጋርዲያን እንደዘገበው የአውሮፓ እግር ኳስ ማኅበር ፕሬዚዳንት አሌክሳንደር ሰፈሪን “ከዚህ በኋላ እግር ኳስ እግር ኳስነቱን ያጣል” ሲልም በሕጉ ላይ ያለውን ተቃውሞ ገልጸዋል።

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here