ለአርሰናል ወሳኙ ግጥሚያ!

0
27
ባሕር ዳር: ታኅሣሥ 30/2018 ዓ.ም (አሚኮ) የእንግሊዝ ፕሪምየር ሊግ በ21ኛ ሳምንት መርሐ ግብር ዛሬ ምሽት 5:00 ላይ አርሰናል በሜዳው ኢምሬትስ ከሊቨርፑል ጋር ይጫወታል።
አርሰናል በሊጉ ካደረጋቸው 20 ጨዋታዎች ውስጥ በ15ቱ አሸንፏል። በሦስት ጨዋታዎች ደግሞ አቻ ተለያይቶ እና በሁለት ጨዋታዎች ተሸንፎ 48 ነጥብ በመሠብሠብ ሊጉን እየመራ ይገኛል።
በደረጃ ሰንጠረዡ በሁለተኛነት የሚከተለው ማንችስተር ሲቲ እና በሦስተኛነት የሚገኘው አስቶንቪላ ትናንት ነጥብ መጣላቸው ለአርሰናል ሰርግ እና ምላሽ ኾኖለታል።
የአርሰናሉ አሠልጣኝ ሚኬል አርቴታ“ ከሊቨርፑል ጋር የምናደርገውን ጨዋታ በጉጉት እየጠበቅነው እንገኛለን፤ ደጋፊዎቻችን የተለዬ ድባብ እንዲፈጥሩ ለማድረግ እንጫወታለን ብለዋል።
ሊቨርፑል በአንጻሩ ከ20 ጨዋታዎች ውስጥ በ10 አሸንፏል። በአራቱ ደግሞ አቻ ተለያይቶ እና በስድስቱ ተሸንፎ 34 ነጥብ በመያዝ አራተኛ ነው።
የሊቨርፑል አሠልጣኝ አርኔ ስሎት ቡድኑ የታሰበውን ያክል ነጥብ አልሠበሠበም በሚል ከደጋፊዎች ከፍተኛ ትችትን እያስተናገዱ ባለበት ሰዓት ነው የሊጉን ጠንካራ ቡድን የሚገጥሙት።
ይህ ደግሞ በጨዋታው ላይ አሉታዊ ተጽዕኖ ማሳረፉ አይቀሬ ነው እየተባለ ይገኛል።
ሁለቱ ቡድኖች እንደ አውሮፖ አቆጣጠር ከ1995 ወዲህ በ74 ጨዋታዎች ተገናኝተው ሊቨርፑል በ27 በማሸነፍ የበላይ ነው። አርሰናል ደግሞ በ20 ጨዋታዎች አሸንፏል።
በኢምሬትስ ስታዲየም ከተደረጉ 35 ጨዋታዎች ሊቨርፑል ያሸነፈው በዘጠኝ ጨዋታዎች ብቻ ሲኾን በ13ጨዋታዎች አርሰናል አሸንፏል። በ13 ጨዋታዎች ደግሞ አቻ ተለያይተዋል።
ሁለቱ ቡድኖች ካላቸው ስም እና ዝና እንዲሁም ወቅታዊ አቋም አንጻር ዛሬ ጠንካራ ጨዋታ ያደርጋሉ ተብሎ በጉጉት ተጠብቋል።
በሊጉ ትናንት በነበሩ ጨዋታዎች ቦርንማውዝ ቶትንሃምን 3ለ2፣ ብሬንት ፎርድ ሰንደርላንድን 3ለ0፣ ፉልሃም ቼልሲን 2ለ1፣ ኒውካስትል ሊድስን 4ለ3 አሸንፈዋል።
ክሪስታል ፓላስ ከአስቶን ቪላ 0ለ0፣ ኤቨርተን ከዎልቭስ 1ለ1፣ ማንቸስተር ሲቲ ከብራይተን 1ለ1፣በርንሌይ ከማንቸስተር ዩናይትድ 2ለ2 መለያየታቸውን ይታወሳል።
በሙሉጌታ ሙጨ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here