ባሕር ዳር: ታኅሣሥ 28/2018 ዓ.ም (አሚኮ) ሞሮኮ ባዘጋጀችው በ35ኛው የአፍሪካ ዋንጫ ዛሬ በጥሎ ማለፍ ጨዋታ አልጀሪያ ከዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ እንዲሁም ኮትዲቯር ከቡርኪናፋሶ ይጫወታሉ።
አልጀሪያ እና ዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ በስታዲ ንጉሥ ሙላይ አል ሀሰን ስታዲየም ምሽት1:00 ላይ ነው የሚጫወቱት።
አልጀሪያ በዚህ ውድድር ያደረገቻቸውን ሦስት ጨዋታዎች በማሸነፍ እና ዘጠኝ ነጥብ በመሠብሠብ ነው ለጥሎ ማለፉ ጨዋታ የደረሰችው።
የአልጀሪያ አብዛኞቹ ተጫዋቾች በአውሮፖ፣ እስያ እና አፍሪካ ቡድኖች እየተጫወቱ ይገኛሉ።
ዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎም ካደረጋቸው ሦስት ጨዋታዎች በሁለቱ አሸንፎ እና በአንዱ አቻ ተለያይቶ ሰባት ነጥብ በመያዝ ከምድቡ በሁለተኛነት አጠናቅቆ ነው ለጥሎ ማለፍ የደረሰው። የብሔራዊ ቡድኑ አብዛኞቹ ተጫዋቾች ፕሮፌሽናል ናቸው።
አልጀሪያ እና ዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ በታሪክ በተገናኙባቸው ሰባት ጨዋታዎች አልጀሪያ በሦስቱ ስታሸንፍ በአራት ጨዋታዎች ደግሞ አቻ ተለያይተዋል።
ምሽት 4:00 ደግሞ ኮትዲቮር ከቡርኪናፋሶ በስታዲ ዴ ማራካሽ ስታዲየም ይጫወታሉ።
ኮትዲቮር ካደረገቻቸው ሦስት ጨዋታዎች በሁለቱ አሸንፋለች። በአንድ ጨዋታ ደግሞ አቻ በመለያዬት ሰባት ነጥብ በመሠብሠብ ምድቡን በአንደኛነት ነው ያጠናቀቀችው።
ቡርኪና ፋሶ ደግሞ ከሦስት ጨዋታዎች በሁለቱ አሸንፋ፣ በአንድ ጨዋታ በመሸነፍ እና ስድስት ነጥብ በመያዝ በሁለተኛነት አጠናቃ ነው ለጥሎ ማለፉ የደረሰችው።
ሁለቱ ሀገራት ካላቸው ወቅታዊ አቋም አንጻር ዛሬ ለመሸናነፍ ጠንካራ ጨዋታ ያደርጋሉ ተብሎ ይጠበቃል።
በሙሉጌታ ሙጨ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!



