ባሕር ዳር: ታኅሣሥ 28/2018 ዓ.ም (አሚኮ) የእንግሊዝ ፕሪምየር ሊግ ዛሬ በ21ኛው ሳምንት መርሐ ግብር ዌስትሃም ዩናይትድ በሜዳው ኖቲንግሃም ፎረስትን ምሽት 5:00 ላይ ይጋብዛል።
ዌስትሃም ዩናይትድ በሊጉ ከ20 ጨዋታዎች ማሸነፍ የቻለው በሶስት ጨዋታዎች ብቻ ነው። ቡድኑ 14 ነጥብ በመያዝ ወራጅ ቀጣናው ላይ ይገኛል።
የዛሬውን ጨዋታ ካሸነፈ ከወራጅ ቀጣናው ባይወጣም በቀጣይ ከሚኖረው ውጤት ላይ ተመርኩዞ ደረጃውን ለማሻሻል ያግዘዋል።
ኖቲንግሃም ፎረስትም በሊጉ ከ20 ጨዋታዎች ያሸነፈው በአምስት ጨዋታዎች ብቻ ነው። 18 ነጥብ ይዞም ከወራጅ ቀጣናው ፈቀቅ ያለው ለጥቂት ነው። ስለኾነም ጨዋታውን ማሸነፍ ደረጃውን በአንድ አሻሽሎ ከወራጅ ቀጣናው እንዲርቅ ያደርገዋል።
ሁለቱ ክለቦች እንደ አውሮፖ አቆጣጠር ከ1995 ወዲህ በ21 ጨዋታዎች ተገናኝተው በ11ዱ ዌስትሃም ሲያሸንፍ በሰባቱ ኖቲንግሃም ድል አድርጓል። በሦስት ጨዋታዎች ደግሞ አቻ ተለያይተዋል።
በፕሪምየር ሊጉ ደግሞ በ13 ጨዋታዎች ተገናኝተው ዌስትሃም በስድስቱ አሸንፏል። ኖቲንግሃም በአምስት ጨዋታዎች ድል ነስቷል። በሁለት ጨዋታዎች ደግሞ አቻ ተለያይተዋል።
የሁለቱ ቡድኖች ደረጃ ቡድኖቹ በተቀራራቢ አቋም ላይ እንደሚገኙ ይጠቁማል።
ዌስትሃም በወራጅ ቀጣናው እንደመገኘቱ እና ኖቲንግሃም 17ኛ ደረጃ ላይ በመገኘቱ ብርቱ ፉክክር ያደርጋሉ ተብሎ ይጠበቃል።
ሊጉን አርሰናል በ48 ነጥብ ይመረዋል፤ ማንቸስተር ሲቲ እና አስቶን ቪላ በ42 ነጥብ በግብ ክፍያ ተበላልጠው ይከተሉታል። ዌስትሃም፣ በርንሌይ እና ወልቭስ ወራጅ ቀጣናው ላይ ተቀምጠዋል።
በሙሉጌታ ሙጨ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!



