ማን ይወርዳል? ማንስ ይተርፋል?

0
38
ባሕር ዳር: ታኅሣሥ 27/2018 ዓ.ም (አሚኮ) በቁጥር 20 ክለቦችን የሚያሳትፈው የእንግሊዝ ፕሪምየር ሊግ የጎርጎሮሳውያኑን አዲስ ዓመት (2026) ሲቀበል ማካኼድ ካለባቸው 38 ጨዋታዎች ውስጥ ግማሽ ያህሉን ሁሉም ክለቦች አከናውነዋል፡፡
ወልቭስ ከ19 ጨዋታዎች ሦስት ነጥቦችን ብቻ አስመዝግቦ አዲሱን ዓመት የተቀበለ ክለብ ኾኗል፡፡
በእንግሊዝ ፕሪምየር ሊግ ታሪክ ከ19 ጨዋታዎች ሦስት ነጥቦችን ብቻ በማስመዝገብ የሁለት ጊዜ ባለታሪኩም ይሄው የወልቭስ ክለብ ነው፡፡
ወልቭስ በ2003/04 የውድድር ዘመን ከ19 ጨዋታዎች አንድ አሸንፎ እና በ18 ተሸንፎ በግማሽ ጨዋታ የዝቅተኛ ውጤት ክብረ ወሰን ነበረው፡፡
ወልቭስ በዘንድሮው የ2025/26 የውድድር ዘመንም ከ19 ጨዋታ በሦስት ጨዋታዎች አቻ ወጥቶ በድጋሚ የራሱን የዝቅተኛ ውጤት ክብረ ወሰን ደግሞታል፡፡
ሰንደርላንድ በ2002/03 የውድድር ዘመን ከ19 ጨዋታዎች አምስት ነጥቦችን ብቻ አስመዝግቧል፡፡ በአንዱ አሸንፎ፣ በሁለት አቻ ተለያይቶ እና በ16 ተሸንፎ ነው ከ19 ጨዋታዎች አምስት ነጥብ ብቻ ያስመዘገበው፡፡
ደርቢ ካውንቲ በ2007/08 የውድድር ዘመን አንድ አሸንፎ፣ በሦስት አቻ ተለያይቶ እና በ15 ጨዋታዎች ተሸንፎ ከ19 ጨዋታዎች ስድስት ነጥቦችን ብቻ በማግኘት ሦስተኛ ዝቅተኛ ውጤት ያስመዘገበ ክለብ ኾኖ ተመዝግቧል፡፡
አሁን በፕሪምየር ሊጉ ሦስተኛ ደረጃ ላይ የሚገኘው አስቶን ቪላ በ2015/16 የውድድር ዘመን ከ19 ጨዋታዎች ማስመዝገብ የቻለው ስምንት ነጥቦችን ብቻ ነበር፡፡
አስቶን ቪላ በዚሁ የውድድር ዘመን በአሠልጣኝ ቲም ሼሪውድ እየተመራ የፕሪሚምየር ሊጉን የመጨረሻ ደረጃ ይዞ አጠናቋል፡፡
ወልቭስ በ2003/04፣ ሰንደርላንድ በ2002/03፣ ደርቢ ካውንቲ በ2007/08 እንዲሁም አስቶን ቪላ በ2015/16 በ19 ጨዋታዎች ዝቅተኛ ውጤት ባስመዘገቡባቸው ዓመታት አራቱም የመጨረሻውን 20ኛ ደረጃ ይዘው ወደ ታችኛው ሊግ ወርደዋል፡፡
በእንግሊዝ ፕሪምየር ሊግ ታሪክ በግማሽ ጨዋታዎች ከአምስት እስከ ስምንት ነጥብ ያገኙት ክለቦች አብዛኛዎቹ ወደ ታችኛው ሊግ መውረዳቸውንም የኢኤስፒኤን መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡
ከ19 ጨዋታዎች ከ10 ነጥብ በታችም በእንግሊዝ ፕሪምየር ሊግ ለመቆየት ዋስትና ኖሮት እንደማያቅም ነው ዘገባው የሚያመላክተው፡፡
በዘንድሮው የእንግሊዝ ፕሪሚየር ሊግ ከ19 ጨዋታ ወልቭስ ሦስት፣ በርንሌይ 12 እና ዌስትሃም ዩናይትድ 14 ነጥቦችን አስመዝግበው በወራጅ ቀጠና ውስጥ ተቀምጠዋል፡፡
ወልቭስ በ20ኛው ሣምንት የእንግሊዝ ፕሪሚየር ሊግ ዌስትሃምን 3 ለ 0 በማሸነፍ ነጥቡን ወደ ስድስት አሳድጓል፡፡ በርንሌይ እና ዌስትሃም ደግሞ ቀድሞ በነበራቸው 12 እና 14 ነጥብ ላይ ተቀምጠዋል፡፡
እስከ18ኛው ሳምንት ድረስ ሁለት ነጥቦች ብቻ የነበሩት ወልቭስ በ19ኛው ሣምንት ከማንቸስተር ዩናይትድ ላይ አንድ ነጥብ አግኝቶ በ20ኛው ሣምንት ደግሞ በሜዳው ከዌስትሃም ዩናይትድ ሦስት ነጥብ ማግኘት ችሏል፡፡ በ18 ጨዋታ ሁለት ነጥብ፣ በሁለት ጨዋታ ደግሞ አራት ነጥብ ማግኘት እንደማለት ነው፡፡
ለመኾኑ ወልቭስን ጨምሮ በርንሌይ እና ዌስትሃም ዩናይትድ ከ21ኛው ሣምንት ጀምረው ውጤታቸውን በማሻሻል ከወራጅ ቀጠናው ያመልጡ ይኾን? ምላሹን ቀጣዮቹ ጨዋታዎች ይነግሩናል፡፡
ዘጋቢ፡- እሱባለው ይርጋ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here