ባሕር ዳር: ታኅሣሥ 27/2018 ዓ.ም (አሚኮ) 35ኛው የአፍሪካ ዋንጫ የጥሎ ማለፍ ጨዋታ ዛሬ ሲቀጥል ግብጽ ከቤኒን እንዲሁም ናይጀሪያ ከሞዛምቢክ ይጫወታሉ።
ምሽት 1:00 ግብጽ እና ቤኒን በስታዲ ደ’አጋዲር ስታዲየም ይጫዎታሉ። ሁለቱ ሀገራት እንደ አውሮፖ አቆጣጠር ከ2005 ወዲህ በተገናኙባቸው ሦሥት ጨዋታዎች ግብጽ በሁሉም ጨዋታዎች አሸንፋለች።
በእነዚህ ጨዋታዎች 13 ግቦች መረብ ላይ ያረፉ ሲኾን ግብጽ 11 ግብ አስቆጥራለች። ቤኒን በግብጽ መረብ ላይ ሁለት ግብ ብቻ ነው ማስቆጠር የቻለችው።
ግብጽ በ35ኛው የአፍሪካ ዋንጫ ካደረገቻቸው ሦሥት ጨዋታዎች በሁለቱ አሸንፋ እና በአንዱ አቻ ተለያይታ ሰባት ነጥብ በመያዝ ነው ለጥሎ ማለፍ የደረሰችው።
ግብጽ በዛሬው ጨዋታ 4_3_3 አሰላለፍን ትተገብራለች የሚሉ መረጃዎች ወጥተዋል።
ግብጽ በሊበርፑሉ ሞሐመድ ሳላህ እና በማንቸስተር ሲቲው ኦማር ማርሙሽ ትመራለች ነው የተባለው።
ተጋጣሚዋ ቤኒን በ35ኛው የአፍሪካ ዋንጫ ካደረገቻቸው ሦሥት ጨዋታዎች በአንዱ ብቻ ነው ማሸነፍ የቻለችው።
በሁለት ጨዋታ ተሸንፋ ሦሥት ነጥብ በመያዝ በጥሩ ሦሥተኛነት ነው ለጥሎ ማለፍ ጨዋታ የደረሰችው።
የቤኒን ብሔራዊ ቡድን ከግብጽ በበለጠ ኹኔታ አብዛኞቹ ተጫዋቾች በአውሮፓ፣ እስያ እና አፍሪካ በሚገኙ ስመ ጥር ቡድኖች የሚጫወቱ ናቸው።
በሌላ ጨዋታ ምሽት 4:00 ናይጀሪያ ከሞዛምፒክ በኮምፕሌክስ ስፖርቲፍ ዴ ፌስ ስታዲየም ይጫዎታሉ።
ሁለቱ ሀገራት በቅርብ ባደረጓቸው አምስት ጨዋታዎች ናይጀሪያ በአራቱ ስታሸንፍ በአንድ ጨዋታ አቻ ተለያይተዋል።
የአፍሪካ ዋንጫን ሦሥት ጊዜ ያነሳችው ናይጀሪያ ሁሉም በሚባል ኹኔታ ተጫዋቾቿ ፕሮፌሽናል ናቸው።
በዚህ የአፍሪካ ዋንጫ ናይጀሪያ ያደረገቻቸውን ሦሥት ጨዋታዎች ማሸነፍ ችላለች።
ናይጀሪያ ዛሬ 4_3_1_2 አሰላለፍን በመጠቀም በአሳማኝ ጨዋታ ሩብ ፍጻሜውን ትቀላቀላለች ብለው የገመቱ ጥቂት አይደሉም።
ተጋጣሚዋ ሞዛምቢክ ጥቂት ተጫዋቾቿ ናቸው በፕሮፌሽናል ደረጃ እየተጫወቱ የሚገኙት።
ብሔራዊ ቡድኑ ካደረጋቸው ሦሥት ጨዋታዎች በአንዱ አሸንፎ፣ በሁለቱ ተሸንፎ ነው ዛሬ ናይጀሪያን የሚገጥመው።
ሞዛምፒክ በ4_2_3_1 አሰላለፍ ነው ናይጀሪያን የሚገጥመው።
ቡድኑ እያሳየ ካለው ወቅታዊ አቋም አንጻር ግን ዛሬ ናይጀሪያን ይፈትናል ተብሎ እንደማይጠበቅ ነው ዴይሊ ሜይል የዘገበው።
በሙሉጌታ ሙጨ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!



