ማንቸስተር ሲቲ ወይስ ቼልሲ?

0
78
ባሕር ዳር: ታኅሣሥ 26/2018 ዓ.ም (አሚኮ) በ20ኛ ሳምንት የእንግሊዝ ፕሪሚየር ሊግ መርሐ ግብር ዛሬ ምሽት 2:30 ላይ ማንቸስተር ሲቲ ከቼልሲ ጋር የሚያደርጉት ጨዋታ ተጠባቂ ኾኗል፡፡
ሁለቱ ቡድኖች እንደ አውሮፖ አቆጣጠር ከ1995 ወዲህ በተገናኙባቸው 50 የፕሪሚየር ሊግ ጨዋታዎች ቼልሲ በ24 ጨዋታዎች በማሸነፍ የበላይነቱን ይዟል።
ማንቸስተር ሲቲ ቼልሲን ያሸነፈው በ19 ጨዋታዎች ነው። በሰባቱ ደግሞ አቻ ነው የተለያዩት።
ሁለቱ ቡድኖች ከ1995 ጀምሮ በአጠቃላይ በ64 ጨዋታዎች ተገናኝተዋል። በተለይ በኢትሃድ ስታዲየም ካደረጉት 34 ጨዋታዎች ማንቸስተር ሲቲ በ20 ጨዋታዎች በማሸነፍ የበላይነቱን ወስዷል።
በአንጻሩ በስታምፎርድ ብሪጅ ስታዲየም ባደረጓቸው 30 ግጥሚያዎች ቼልሲ በ15ቱ አሸንፏል።
በኤፍ ኤ ካፕ መርሐ ግብር በስድስት ጨዋታዎች ተገናኝተው ማንቸስተር ሲቲ በአራቱ ሲያሸንፍ ቼልሲ ድል የቀናው በሁለቱ ብቻ ነው።
ዛሬስ በሚገናኙበት የፕሪሚየር ሊግ ጨዋታ ማን ያሸንፍ ይኾን?
አሠልጣኙን ያሰናበተው ቼልሲ በጊዜያዊው አሠልጣኝ ካሉም ማክ ፋርላን እየተመራ ነው ወደ ኢትሃድ ስታዲየም የተጓዘው።
ቼልሲ ካለፉት ስድስት የፕሪምየር ሊግ ጨዋታች ማሸነፍ የቻለው በአንድ ጨዋታ ብቻ ነው። በመኾኑም ዛሬም በማንቸስተር ሲቲ ከፍተኛ ፈተና ይጠብቀዋል እየተባለ ነው።
ቼልሲ በዛሬው ጨዋታ ሞይሰስ ካይሴዶን በቅጣት አያሰልፍም።
ተጋጣሚው ማንቸስተር ሲቲ ከሊጉ መሪ አርሰናል በሰባት እንዲሁም በአስቶን ቪላ በአንድ ነጥብ ተበልጦ በሦሥተኛነት ተቀምጧል። ዛሬ ወደ አሸናፊነት በመመለስ የደረጃም የነጥብ ልዩነትም ለመፍጠር ብርቱ ፉክክር የሚያደርግ ይኾናል።
ዜጎቹ ጨዋታውን ማሸነፍ አንድም ከአርሰናል ጋር ያለውን የነጥብ ልዩነት በአራት እንዲያጠቡ እና በሁለተኛነት እንዲቀመጡ ሲያስችላቸዋል። ጨዋታውን በአቻ ውጤት ካጠናቀቁም አስቶን ቪላን በግብ ክፍያ በመብለጥ የሁለተኛነት ደረጃን ይይዛሉ።
ዜጎቹ በጨዋታው ጆን ስቶንስ፣ ኦስካር ቦብ እና ማቲዮ ኮቫቺች በጉዳት የማያሰልፏቸው ተጫዋቾች ናቸው።
በሌላ ጨዋታ ቀን 9:30 ማንቸስተር ዩናይትድ እና ሊድስ ዩናይትድ ይጫወታሉ።
ምሽት 12:00 ደግሞ ኤቨርተን ከብሬንትፎርድ፣ ፉልሃም ከሊቨርፑል፣ ኒውካስትል ዩናይትድ ከክሪስታል ፓላስ፣ ቶትንሃም ከሰንደርላንድ ጨዋታቸውን ያደርጋሉ።
በሙሉጌታ ሙጨ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here