ባሕር ዳር: ታኅሣሥ 26/2018 ዓ.ም (አሚኮ) በኢትዮጵያ ከፍተኛ ሊግ የምድብ “ለ” 10ኛ ሳምንት መርሐ ግብር ዛሬ ወሳኝ ጨዋታ ያስተናግዳል።
ቀን 9:30 የአማራ ክልል ተወካይ የኾነው ደሴ ከተማ ከመንጌ ቤላሻንጉል ጋር በጅማ ስታዲየም ይጫወታል።
ደሴ ከተማ እስካሁን ዘጠኝ ጨዋታዎችን አድርጎ 13 ነጥብ እና በአራት ንጹህ የግብ ክፍያ በደረጃ ሰንጠረዡ በአራተኛነት ተቀምጧል።
በ2017 የውድድር ዘመን ቡድኑ ፕሪሚየር ሊግ ለመግባት ከጫፍ ደርሶ በነገሌ አርሲ መበለጡ አይዘነጋም።
ደሴ ከተማ የዛሬውን ጨዋታ ካሸነፈ የሁለተኛነት ደረጃን የሚይዝ ይኾናል።
ተጋጣሚው መንጌ ቤላሻንጉል እስካሁን ስምንት ጨዋታዎችን አድርጓል። 14 ነጥብ እና ሦሥት የግብ ክፍያ በመያዝ በሁለተኛነት ይገኛል።
ሁለቱ ቡድኖች ካላቸው ወቅታዊ አቋም እና የነጥብ መቀራረብ አንጻር ዛሬ የሚያደርጉት ጨዋታ ወሳኝም አጓጊም ኾኗል።
ምድብ “ለ”ን ሀላባ ከተማ በአንደኛነት ይመራዋል። መንጌ ቤላሻንጉል ሁለተኛ ሲኾን አዲስ ከተማ ክፍለ ከተማ በሦሥተኛነት ይከተላል።
የአማራ ክልል ተወካዮቹ ደሴ ከተማ አራተኛ እንዲሁም ደብረ ብርሃን ከተማ በአምስተኛ ደረጃ ላይ ይገኛሉ።
ደሴ ከተማ ከመንጌ ቤላሻንጉል የሚያደርጉትን ጨዋታ ፊፋ ፕላስ በቀጥታ ያሰራጨዋል።
በሙሉጌታ ሙጨ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!



