ባሕር ዳር: ታኅሣሥ 23/2018 ዓ.ም (አሚኮ) በእንግሊዝ ፕሪምዬር ሊግ የ19ኛ ሳምንት መርሐ ግብር ዛሬ አራት ጨዋታዎች ይደረጋሉ።
ምሽት 5:00 ላይ ሰንደርላንድ ማንቸስተር ሲቲን በሜዳው የሚጋብዝበት ጨዋታም ተጠባቂ ኾኗል።
ሁለቱ ቡድኖች እንደ አውሮፓውያን አቆጣጠር ከ2000 ወዲህ በ30 ጨዋታዎች ተገናኝተው ማንቸስተር ሲቲዎች በ22 ጨዋታዎች በማሸነፍ የበላይ ናቸው።
ጥቋቁር ድመቶች በአንጻሩ በአምስት ጨዋታዎች ድል አድርገዋል። በሦስት ጨዋታዎች ደግሞ አቻ ነው የተለያዩት። ከ30 ጨዋታዎች መካከል 27ቱ የፕሪምዬር ሊግ ጨዋታዎች ናቸው። ማንቸስተር ሲቲ በ19 በማሸነፍ ከፍ ብሎ ተቀምጧል። ሰንደርላንድ ያሸነፈው በአምስት ጨዋታዎች ብቻ ነው። በሦስቱ ደግሞ አቻ ተለያይተዋል።
ሰንደርላንድ በ2025/2026 የውድድር ዘመን ካደረጋቸው 18 የፕሪምዬር ሊግ ጨዋታዎች በሰባቱ አሸንፎ፣ በሰባቱ አቻ ተለያይቶ፣በአራቱ ተሸንፎ እና ሁለት የግብ ክፍያ በመያዝ በ28 ነጥብ ሰባተኛ ደረጃ ላይ ይገኛል።
ቡድኑ በዚህ ዓመት በሜዳው ያደረጋቸውን ጨዋታዎች ባለመሸነፍም የታሪክ ባለቤት ነው። ይህን ጥንካሬውንም ዛሬ በውኃ ሰማያዊዎቹ ላይ ይደግመዋል ወይስ ይሸነፋል የሚለው ተጠባቂ ነው።
ጥቋቁር ድመቶቹ (ሰንደርላንድ) ስድስት ያህል ወሳኝ ተጨዋቾቹን በአፍሪካ ዋንጫ ምክንያት ማጣቱ ደግሞ ለሲቲዎች እንደ ጥሩ አጋጣሚ ይቆጠራል።
ሲቲ ከ18 የፕሪምዬር ሊግ ጨዋታዎች የተሸነፈው እንደ ሰንደርላንድ ሁሉ በአራት ጨዋታዎች ብቻ ነው። በአንድ ጨዋታ አቻ ተለያይቶ እና በ13 ጨዋታዎች አሸንፎ የሊጉ መሪ አርሰናል ከያዘው 45 ነጥብ በአምስት ነጥብ ዝቅ ብሎ በሁለተኛነት ተቀምጧል።

ማንቸስተር ሲቲ ከሰንደርላንድ ጋር ያደረጋቸውን ያለፉት አምስት ጨዋታዎች በሙሉ በማሸነፍ የበላይ ነው።
ማንቸስተር ሲቲ ታዲያ ዛሬ ከሊጉ መሪ አርሰናል ያለውን የነጥብ ልዩነት በሁለት ነጥብ ለማጥበብ እና የአሸናፊነት ታሪኩን በወጥነት ለማስቀጠል ይፋለማል።
በማንቸስተር ሲቲ በኩል ጆን ስቶንስ እና ኦስካር ቦብ በጉዳት ምክንያት የማይሰለፉ ተጫዋቾች ናቸው።
በሌሎች ጨዋታዎች ምሽት 2:30 ላይ ክሪስታል ፓላስ ከፉልሃም፣ ሊቨርፑል ከሊድስ ዩናይትድ ይጫወታሉ።
ምሽት 5:00 ላይ ደግሞ ብሬንትፎርድ ከቶትንሃም ሆትስፐር ጨዋታቸውን ያደርጋሉ ሲል ቢቢሲ ዘግቧል።
በሙሉጌታ ሙጨ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!



