ባሕርዳር፡ ታኅሣሥ 21/2018ዓ.ም (አሚኮ) 35ኛው የአፍሪካ ዋንጫ ዛሬ አራት ጨዋታዎችን ያስተናግዳል። ምድብ ሦሥት ላይ ምሽት 1:00 ታንዛኒያ ከቱኒዚያ እንዲሁም ኡጋንዳ ከናይጀሪያ ይጫወታሉ።
ቱኒዚያ በአፍሪካ ዋንጫ ካደረገቻቸው ሁለት ጨዋታዎች በአንዱ አሸንፋ፣ በሌላው ተሸንፋ እና ሦሥት ነጥብ በመያዝ በሁለተኛነት ተቀምጣለች።
ታንዛኒያ በበኩሏ በአንድ ጨዋታ አቻ ተለያይታ፣ በአንዱ ተሸንፋ እና አንድ ነጥብ ብቻ በመያዝ ሦሥተኛ ደረጃን ይዛለች።
ታንዛኒያ እና ቱኒዚያ እንደ አውሮፖ አቆጣጠር ከ2020 ወዲህ በሁለት ጨዋታዎች ተገናኝተው ቱኒዚያ በአንዱ ብቻ አሸንፋለች። በአንድ ጨዋታ አቻ ተለያይተዋል።
ታንዛኒያ ቱኒዚያን ብታሸንፍ በሁለተኛነት ለማለፍ የኡጋንዳን ውጤት መጠበቅ ግድ ይላታል። ኡጋንዳም ተመሳሳይ ነጥብ ኑሯት በግብ ዕዳ ስለሚለያዩ የተሻለ የግብ ልዩነት ያለው ሀገር ኀላፊ ይኾናል።
ኡጋንዳ ከሁለት ጨዋታ በአንዱ አቻ ተለያይታ፣ በአንዱ ተሸንፋ፣ አንድ ነጥብ እና ሁለት የግብ ዕዳ በመያዝ ከምድቡ መጨረሻ ላይ ትገኛለች።
ተጋጣሚዋ ናይጀሪያ ከወዲሁ ስድስት ነጥብ በመሠብሠብ ጥሎ ማለፉን ተቀላቅላለች።
በምድብ አራት ጨዋታ ደግሞ ሦሥት ነጥብ ያላት ቤኒን አራት ነጥብ ከያዘችው ሴኔጋል ምሽት 4:00 ትጫወታለች።
በተመሳሳይ ሰዓት ከምድቡ በሁለት ጨዋታ ተሸንፋ የተሰናበተችው ቦትስዋና አራት ነጥብ ከሰበሰበችው ዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ ትገጥማለች።
ቢቢሲ እንዳስነበበው ጨዋታው ከቦትስዋና በስተቀር የሚገኙ ሀገራት ካሸነፉ ጥሎ ማለፉን ስለሚቀላቀሉ ጨዋታው የሞት ሽረት ፍልሚያ እንደሚያደርገው ይጠበቃል።
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!



