አርሰናል አስቸጋሪ ተጋጣሚውን ምሽት ይጋብዛል።

0
63
ባሕር ዳር: ታኅሣሥ 21/2018 ዓ.ም (አሚኮ) በእንግሊዝ ፕሪምየር ሊግ የ19ኛ ሳምንት መርሐ ግብር ዛሬ ምሽት ስድስት ጨዋታዎች ይደረጋሉ፡፡
ከእነዚህ ጨዋታዎች መካከል አርሰናል እና አስቶንቪላ ምሽት 5:15 ላይ በኢምሬትስ ስታዲየም የሚያደርጉት ጨዋታ ከቡድኖቹ ወቅታዊ አቋም አኳያ ከፍተኛ ግምት ተሰጥቶታል።
አርሰናል በሊጉ 18 ጨዋታዎችን አድርጎ በ13ቱ አሸንፏል። በሦስቱ ጨዋታዎች አቻ ተለያይቷል። በሁለት ጨዋታዎች ደግሞ ተሸንፏል። መድፈኞቹ 22 ንጹሕ የግብ ክፍያ እና 42 ነጥብ በመያዝ ሊጉን እየመሩ ነው።
ቡድኑ ካደረጋቸው 18 ጨዋታዎች አራት ተጨዋቾቹ ከአራት እስከ አምስት ግብ በማስቆጠር ከፍተኛ ግብ አስቆጣሪ በመኾን ተመዝግበዋል።
የአርሰናሉ አሠልጣኝ ሚኬል አርቴታ ጨዋታው ከባድ እና ማራኪ ይኾናል ነው ያሉት። ማሸነፍ የሚያስችል ዝግጅት አድርገናል ያሉት አርቴታ “ዋንጫው የእኛ ነው!” ሲሉም ማሸነፍ እንደሚችሉ አስረግጠው ተናግረዋል።
ተጋጣሚው አስቶንቪላም 18 ጨዋታዎችን አድርጎ በ12 ጨዋታዎች ድል ነስቷል። በሦስቱ አቻ በመውጣት እና በሦስቱ በመሸነፍ 10 የግብ ክፍያ በመያዝ ከአርሰናል በሦስት ነጥብ ዝቅ ብሎ በሦስተኛነት ተቀምጧል።
የቡድኑ አራት ተጨዋቾች ከአራት እስከ ሰባት ግብ በማስቆጠር በከፍተኛ ግብ አስቆጣሪነት ላይ ተመዝግበዋል። ሁለቱ ቡድኖች በታሪክ በ206 ጨዋታዎች ተገናኝተው አርሰናል በ88 ጨዋታዎች በማሸነፍ የበላይ ነው።
አስቶን ቪላም 72 ጨዋታዎችን ማሸነፍ ችሏል። በ46 ጨዋታዎች አቻ ተለያይተዋል። ሁለቱ ቡድኖች በፕሪምየር ሊጉ እርስ በርስ ካደረጓቸው ያለፉት አምስት ጨዋታዎች አስቶን ቪላ ሦስት ጊዜ በማሸነፍ የበላይ ነው። አርሰናል አንዱን አሸንፎ በአንዱ አቻ ተለያይቷል፡፡
የአስቶንቪላው አሠልጣኝ ኡናይ ኢሜሪ” ዓላማችን ዋንጫ መውሰድ አይደለም ብለዋል። የምንጫወተው ግን ለማሸነፍ ነው ብለዋል።
በሌሎች ጨዋታዎች ምሽት 4:15 ላይ በርንሌይ ከኒውካስትል ዩናይትድ፣ ቼልሲ ከቦርንማውዝ፣ ኖቲንግሃም ፎሬስት ከኤቨርተን፣ ዌስትሃም ዩናይትድ ከብራይተን ጋር ይጫወታሉ።
ምሽት 5:15 ላይ ደግሞ ማንቼስተር ዩናይትድ ከወልቭስ ኦልድትራፎርድ ላይ ይገኛሉ።
በሙሉጌታ ሙጨ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here