ባሕርዳር፡ ታኅሣሥ 21/2018ዓ.ም (አሚኮ) የፊፋው ፕሬዚዳንት ጂያኒ ኢንፋንቲኖ በ2026ቱ የዓለም ዋንጫ ዙሪያ የሚነሱ የትኬት ዋጋ ቅሬታዎችን አስመልክተው በሰጡት ምላሽ ታይቶ የማይታወቅ እጅግ ከፍተኛ የትኬት ፍላጎት እያስተናገዱ መኾኑን ገልጸዋል።
ፕሬወዳንቱ የ300 ዓመታት ሽያጭ በ15 ቀናት መቅረቡን ነው የተናገሩት። ባለፉት 100 ዓመታት የዓለም ዋንጫ ታሪክ ውስጥ በአጠቃላይ የተሸጡት ትኬቶች ብዛት 44 ሚሊዮን ብቻ ነው። ለ2026ቱ አሜሪካ፣ ካናዳ እና ሜክሲኮ ለሚያዘጋጁት ውድድር ግን በ15 ቀናት ውስጥ ብቻ 150 ሚሊዮን የትኬት ጥያቄዎች ቀርበዋል ብለዋል።
ፊፋ ለዚህ ታሪካዊ ውድድር ያዘጋጀው የትኬት መጠን ከ6 እስከ 7 ሚሊዮን ብቻ መኾኑን የጠቀሱት ፕሬዝዳንቱ ካለው እጅግ ከፍተኛ ፍላጎት አንጻር የዋጋ ጭማሪ ተደርጓል በሚል የሚነሱ ቅሬታዎች አግባብነት የሌላቸው መኾኑን አመልክተዋል።
“የቀረበልን የትኬት ፍላጎት መጠን ሲታይ የዋጋ ጭማሪ ጥያቄው ወቅታዊ ሁኔታውን ያላገናዘበ ነው” ሲሉ ጂያኒ ኢንፋንቲኖ ተናግረዋል።
2026ቱ ዓለም ዋንጫ በታሪክ ልዩ ከሚያደርጉት ዋና ዋና ጉዳዮች መካከል ለመጀመሪያ ጊዜ በ48 ሀገራት መካከል የሚደረግ ውድድር ነው።
በአጠቃላይ 104 ጨዋታዎች የሚስተናገዱበት ይሆናል።
ውድድሩ በሦስት ሀገራት (አሜሪካ፣ ካናዳ እና ሜክሲኮ) ውስጥ በ16 ከተሞች እንደሚከናወን ኤን ፒአር ዶት አርግ አስነብቧል።
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!



