ጎንደር: ታኅሣሥ 20/2018 ዓ.ም (አሚኮ) የፋሲል ከነማ ደጋፊዎች ማኅበር “ፍቅሩ ሕዝባዊ ክብሩ ንጉሳዊ”
በሚል መሪ መልዕክት ሰባተኛው ዙር የሩጫ ውድድር ጥር 9/2018 ዓ.ም እንደሚያካሄድ ገልጿል። ውድድሩ ስኬታማ በኾነ መልኩ እንዲካሄድ ቅድመ ዝግጅት እየተደረገ ነው ተብሏል።
የፋሲል ከነማ ደጋፊዎች ማኅበር ፕሬዝዳንት ቴዎድሮስ ብርሃኑ የፋሲል ከነማ ደጋፊዎች ቤተሰባዊ ሩጫ ለማከናወን የተለያዩ ሥራዎች ሲሠሩ መቆየታቸውን አስታውሰዋል።
ለሩጫው አስፈላጊ የኾኑ ስፖንሰሮችን በማፈላለግ የቅድመ ዝግጅት ሥራ መሠራቱንም ገልጸዋል። በዚህ የሩጫ ውድድርም እስከ 15ሺህ የክለቡ ደጋፊዎች እና የስፖርት ቤተሰቦች እንደሚሳተፉ ተናግረዋል። ከሩጫ ውድድሩ ወደ 6 ሚሊዮን ብር ገቢ ለማግኘት መታሰቡንም አንስተዋል።
የሩጫ ውድድሩ መነሻውን ፕላዛ ሆቴል በማድረግ መስቀል አደባባይ ላይ ይጠናቀቃል ተብሏል።
የደጋፊ ማኅበሩ በየዓመቱ የሩጫ ውድድር ከማድረግ ባሻገር አባላቱን ለማሳደግ እና ከአባላቱ የሚገኘውን ገቢ ከፍ ለማድረግ እየሠራ ነው ብለዋል።
ፋሲል ከነማ እግር ኳስ ክለብ ወደ ጎንደር መጥቶ በደጋፊው ፊት እንዲጫወት እየሠሩ እንደሚገኙ የገለጹት ፕሬዝዳንቱ ደጋፊ ማኅበሩ በስታዲየሙ እድሳት ላይ እገዛ እያደረገ እንደሚገኝም ተናግረዋል።
ዘጋቢ፦ ደስታ ካሣ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!



