የአፍሪካ ዋንጫ የግማሽ ፍጻሜ ጨዋታዎች ዛሬ ይካሄዳሉ።

0
375

ባሕር ዳር: ጥር 29/2016 ዓ.ም (አሚኮ) በኮትዲቯሩ የአፍሪካ ዋንጫ ደቡብ አፍሪካ፣ ናይጀሪያ፣ ዲሞክራቲክ ኮንጎ እና አዘጋጇ ኮትዲቯር ግማሽ ፍጻሜውን መቀላቀላቸው ይታወሳል። ለፍጻሜ ለመድረስም ናይጀሪያ ከደቡብ አፍሪካ እና ኮትዲቯር ከዴሞክራቲክ ኮንጎ ይጫወታሉ።

የናይጀሪያ ብሔራዊ ቡድን በዘንድሮው የአፍሪካ ዋንጫ ወጥ ብቃት በማሳየት እየተሞገሰ ነው። የተረጋጋ የተከላካይ ክፍልና ለተጋጣሚ የሚያስቸግር የአጥቂ ክፍሉ ለጥንካሬው ምክንያት ነው እንደ ጎል የመረጃ ምንጭ። በሩብ ፍጻሜው በዚህ ውድድር ጠንካራ የነበረችውን አንጎላን 1 ለ 0 በመርታት ነው ለግማሽ ፍጻሜ የደረሰችው።

የናይጀሪያ ተጋጣሚ ደቡብ አፍሪካ ብዙ ግምት ሳይሰጣት በግማሽ ፍጻሜ ተገኝታለች። በጥሎ ማለፉ የዋንጫ ባለቤት እንደምትኾን የተገመተችው ሞሮኮን 2 ለ 0 ማሸነፏ ብዙዎችን አስገርሟል። በሩብ ፍጻሜ ደግሞ ኬፕ ቨርዴን በመርታት ለዛሬው ጨዋታ ደርሳለች።

በዛሬው ጨዋታ ናይጀሪያ የማሸነፍ ቅድመ ግምት ያገኘች ቢኾንም ደቡብ አፍሪካ ግማሽ ፍጻሜ የደረሰችው በየጨዋታዎቹ የማሸነፍ ግምት ሳይሰጣት ነው። ጨዋታው ምሽት 2 ሰዓት ይጀምራል።

ምሽት 5ሰዓት ደግሞ አዘጋጇ ኮትዲቯር ከዴሞክራቲክ ኮንጎ ይጫወታሉ። ኮትዲቯር ከነበረችበት ደካማ አጀማመር የተሻለ መነቃቃትን ያሳየ ቡድን እያስመለከተች ነው። ከምድቧ ለማለፍ በመቸገሯ አሠልጧኟን ያሰናበተችው ሀገር አሁን ዋንጫውን ማለም ጀምራለች።

በምክትል አሠልጣኝ እየተመራች ጠንካራዎቹ ሴኔጋልን እና ማሊን ድል ማድረጓ ይታወሳል። በተለይ በሩብ ፍጻሜው የጨዋታውን አብላጫ ጊዜ አንድ ተጫዋች በቀይ ካርድ አጥታ ማሸነፍ መቻሏ ደጋፊዎቿን ጮቤ አስረግጧል።

የኮንጎ ብሔራዊ ቡድን በተሻለ የአንድነት መንፈስ እዚህ የደረሰ ቡድን ነው። ጠንካራዋ ግብጽን በመለያ ምት አሸንፎ ሩብ ፍጻሜ ሲደረስ ግማሽ ፍጻሜ ለመድረስም ጊኒን አሸንፏል። የሁለቱ ቡድኖች ጨዋታ ምሽት 5 ሰዓት የሚጀምር ሲኾን የተሻለ የመሸናነፍ ትግል እንደሚታይበት ተጠብቋል።

በአስማማው አማረ

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here