በአፍሪካ ዋንጫ ጨዋታ ዛሬ ወሳኝ ጨዋታዎች ይካሄዳሉ።

0
44
ባሕር ዳር፡ ታኅሣሥ 17/2018 ዓ.ም አሚኮ) 35ኛው የአፍሪካ ዋንጫ ዛሬ አራት ወሳኝ ጨዋታዎችን ያስተናግዳል።
ምድብ አንድ ላይ የሚገኙት ዛምቢያ ከኮሞሮስ ምሽት 2:30 በስታዲ ሞሐመድ አምስተኛ ስታዲየም ጨዋታቸውን ያደርጋሉ።
“የመዳብ ጥይቶች” በሚል ቅጽል ስም የሚጠሩት ዛምቢያዎቹ እንደ አውሮፓ አቆጣጠር በ2012 የአፍሪካ ዋንጫን አንስተዋል።
ዛምቢያ ከማሊ ጋር አንድ አቻ ተለያይታ አንድ ነጥብ በመያዝ በሦሥተኛነት ተቀምጣለች። ኮሞሮስ (አሳዎቹ) ደግሞ በሞሮኮ ተሸንፋ ከምድቡ መጨረሻ ላይ ትገኛለች።
ዛምቢያ ታዲያ ጨዋታውን በማሸነፍ እና ነጥቧን አራት በማድረስ በሁለተኛነት ለመቀመጥ ነው ዛሬ የምትጫወተው።
ኮሞሮስ ደግሞ ሦሥት ነጥብ በመያዝ በፉክክሩ ለመቆየት ብርቱ ፉክክር ታደርጋለች ተብሎ ይጠበቃል።
ሁለቱ ሀገራት እንደ አውሮፓ አቆጣጠር ከ2010 ወዲህ በሰባት ጨዋታዎች ተገናኝተው ዛምቢያ በአራት ጨዋታዎች አሸንፋለች።
ኮሞሮስ ደግሞ በሁለት ጨዋታዎች አሸንፋለች። በአንድ ጨዋታ ደግሞ አቻ ተለያይተዋል።
የዛምቢያ ዋና አሠልጣኝ ሙሳ ሲቾን ኮሞሮስ ፈጣን ተጫዋቾችን የያዘ ቡድን እንደገነባች ተናግረዋል።
በመኾኑም “ዛሬ ጠንካራ ጨዋታ እንደሚጠብቀን አውቀን ጥሩ ዝግጅት አድርገናል” ብለዋል።
የኮሞሮስ ብሔራዊ ቡድን ዋና አሠልጣኝ ስቴፋኖ ኩሲን በበኩላቸው “መነሻችን ስኬታማ ለመኾን ስለኾነ ለማሸነፍ በቁርጠኛነት እንጫወታለን ነው ያሉት።
በሌላ የምድቡ ጨዋታ ምድቡን በሦሥት ነጥብ እና በሁለት የግብ ክፍያ እየመራች የምትገኘው ሞሮኮ አንድ ነጥብ ብቻ ከያዘችው ማሊ ትጫወታለች።
ጨዋታው በስታዲ ልዑል ሙላይ አብዳላህ ስታዲየም ምሽት 5:00 ላይ ይደረጋል።
ምድብ ሁለት ላይ ደግሞ በመጀመርያ ጨዋታ የተሸነፉት ዚምባቡዌ እና አንጎላ ቀን 9:30 ይጫወታሉ።
በዚሁ ምድብ የሰባት ጊዜ የአፍሪካ ዋንጫ አሸናፊዋ ግብጽ (ፈርዖኖች) የአፍሪካ ዋንጫን አንድ ጊዜ ብቻ ካነሳችው ደቡብ አፍሪካ (ባፋና ባፋና) ጋር ምሽት ይጫወታሉ።
ጨዋታው ምሽት 12:00 በስታዲ ደ’አጋዲየር ስታዲየም ይደረጋል።
ሁለቱ ሀገራት ያደረጉትን የመጀመሪያ ጨዋታ በማሸነፍ ሦሥት ነጥብ እና አንድ የግብ ክፍያ በመያዝ ምድቡን እየመሩ ይገኛሉ።
በመኾኑም ጨዋታው ትልቅ ግምት ተሰጥቶታል ሲል ያስነበበው ቢቢሲ ስፖርት ነው።
ዘጋቢ፦ሙሉጌታ ሙጨ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here