በእግር ኳስ ከታዩ አይረሴ ታሪኮች አንዱ..

0
45
ባሕር ዳር፡ ታኅሣሥ 16/2018 ዓ.ም አሚኮ) በእግር ኳሱ ጨዋታ ዓለም አይረሴ ታሪኮች ተጽፈዋል። አንዳንዶቹ አፍን በእጅ የሚያስከድኑ አለፍ ሲል የሚያሳዝኑ ኾነው እናገኛቸዋለን።
ከዛሬ 88 ዓመት በፊት በእንግሊዝ ምድር የኾነውን ታሪክ ወደ ኋላም ተጉዞ ታሪክ ያሳታውሰናል። አሁን ላይ የእንግሊዝ ፕርሚየር ሊግ ከመባሉ አስቀድሞ የመጀመሪያው ዲቪዚዮን የሚል ስያሜ ተሰጥቶት ውድድሩ ሲካሄድ ነበር። ወቅቱ በአውሮፓውያኑ የዘመን ስሌት ታኅሣሥ 25/1937 ነበር።
በ1937/38 የእንግሊዝ ፕርሚየር ሊግ መርሐ- ግብር በቦክሲንግ ደይ ጨዋታ ቸልሲን ከቻርልተን ዩናይትድ ጋር አገናኝቷል። በጨዋታውም በጂሚ ሲድ የሚመራው ቻርልተን ባርትራምን በግብ ጠባቂነት፣ ጆርጅ ግሪን፣ በርት ተርነር፣ ጃክ ሸርቬ፣ ጃክ ኦክስን በተከላካይነት መስመር ያሰለፈ ሲኾን ሌስ ቦልተር፣ ሀሮልድ ሆቢስ የፊት መስመር አጥቂ በመኾን ተሰልፈዋል።
የሁለቱ ቡድኖች ጨዋታ በአንድ አቻ ውጤት እስከ 60ኛው ደቂቃ ድረስ ቢቀጥልም ያልተጠበቀ ክስተት አጋጠመ። ጨዋታውን ሲያስተናግድ የነበረው ስታምፎርድ ብሪጅ ስታዲየም ከየት መጣ ባልተባለ ደመና ተዋጠ።
በዚህ መካከል ጨዋታውን ሲዳኙ የነበሩ የመሐል ዳኛው አንድ ውሳኔ አሳለፉ። በወቅቱ የነበረው የአየር ሁኔታ ከፍተኛ ደመና የፈጠረ በመኾኑ ጨዋታው እንዲቋረጥ ውሳኔ አሳልፊያለሁ አሉ።
በወቅቱ የነበረው ደመና ስታምፎርድ ብሪጅን ወደ ድቅድቅ ጨለማ በመቀየሩ ተጫዋቾች እርስ በእርስ መተያየት ወደማይችሉበት ደረጃ ደርሰው እንደነበር ይነገራል።
ጨዋታው በመቋረጡ ተጫዋቾች ወደ መልበሻ ክፍል ሲያመሩ የሁለቱ ቡድኖች ደጋፊዎች ስታዲየሙን ለቀው ወጡ። ይሁን እንጂ የቻርልተኑ ግብ ጠባቂ ሳሙኤል ባርትራም መረቡን ላለማስደፈር በሚል በግብ ቋሚው መሐል ላይ ከወገቡ ሸብረክ ብሎ ላይ እንደ ጅብራ በመቆም ከፊቱ ካለው ኀይለኛ ደመና ጋር ተፋጧል።
በዚህ ሂደት ሳሙኤል ባርትራምን ህልም ከሚመስለው ዓለም የሰማው ድምጽ ቀሰቀሰው። እንዲህ የሚል ድምጽ “እዚህ ምን እየሠራህ ነው? ጨዋታዉ እኮ ተቋርጧል…”ሲል ጨዋታውን ሲቆጣጠር የነበረ የጸጥታው አስከባሪ ጠየቀው።
ከዓመታት በኋላ ሳሙኤል ባርትራም የግል የሕይወት ታሪኩን በተመለከተ በጻፈው ጹሑፍ ላይ “በዛች ምሽት በነበረው ጨዋታ በደመናው መሐል የተወሰኑ ተጫዎችን እየተመለከትኩ ስለነበረ የእኔ እሳቤ የእኛ ቡድን አጥቅቶ እየተጫወተ መስሎኝ ነበር ይላል።
ባርትራም አክሎም ” ስታዲየሙን የዋጠው ደመና በወቅቱ በጨዋታው ምን እንደተፈጠረ እንዳልረዳ አድርጎኝ ነበር ” ብሏል የተፈጠረውን ክስተት ሲገልጽ።
መረጃዎች እንደሚያሳዩት ጨዋታው ከተቋረጠ በኋላ ለ15 ደቂቃ ያህል ባርትራም ብቻውን በባዶ ሜዳ ቆይቷል።
በ20 ዓመት ዕድሜው ለመጀመሪያ ጊዜ ለቻርልተን ቡድን መሰለፍ የጀመረው ይህ ተጫዋች በቻርልተን ለ22 ዓመት 623 ጨዋታዎች ላይ ተሰልፎ መጫወቱን መረጃዎች ያሳያሉ።
ዘጋቢ፦ሀብታሙ ዳኛቸው
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here