በአንጎላ አዘጋጅነት በተካሄደው ውድድር ኢትዮጵያ ጥሩ ተሞክሮዎች አግኝታለች።

0
48
አዲስ አበባ: ታኅሣሥ 15/2018 ዓ.ም (አሚኮ) የአራተኛውን የአፍሪካ ወጣቶች ኦሎምፒክ ጨዋታዎች ዝግጅ፣ ተሳትፎ እና የአምስተኛው የአፍሪካ ወጣቶች ኦሎምፒክ ጨዋታዎች አዘጋጅነትን በተመለከተ የኢትዮጵያ ኦሎምፒክ ኮሚቴ መግለጫ ሰጥቷል።
በአንጎላ አዘጋጅነት ለ10 ቀናት በተከናወነው ውድድር ኢትዮጵያ ጥሩ ተሞክሮዎች ማግኘቷን የኢትዮጵያ ኦሎምፒክ ኮሚቴ ፕሬዝዳንት አሸብር ወልደጊዮርጊስ (ዶ.ር) ተናግረዋል።
ከክልል እና ከከተማ መሥተዳደሮች ጋር በጋራ መሥራታቸው ውጤቱ እንዲመጣ አስችሏል ያሉት ፕሬዝዳንቱ ባለፉት ኦሎምፒክ ውጤቶች የተከፋውን ሕዝብ ለመካስ ተስፋ የተጣለበት ውጤት መገኘቱን አስገንዝበዋል።
ዶክተር አሸብር በመድረኩ ኢትዮጵያ የ2027 ውድድር የማዘጋጀት ዕድል ማግኘቷን ጠቅሰው ኢትዮጵያ ያገኘችው ዕድል ትልቅ ነው ነገር ግን ብዙ መሥራት እንደሚገባ መገንዘብ ያስፈልጋል ነው ያሉት።
ከአራተኛው የወጣቶች ኦሎምፒክ በተሻለ ውድድሩን ለማዘጋጀት ሰፊ ዝግጅት እንደሚያስፈልግም በመግለጫው ተመላክቷል።
“አፍሪካውያን በጣሉብን ዕምነት ልክ መገኘት አለብን” ያሉት ፕሬዝዳንቱ በአራተኛ የአፍሪካ ወጣቶች ኦሎምፒክ ለተገኘው ስኬት አብርክቶ ለነበራቸው ሁሉ ምሥጋና አቅርበዋል።
አሁን ውጤት ያመጡ ስፖርተኞች የወደፊት የኢትዮጵያ ተስፋ መኾናቸውን ያነሱት ዶክተር አሸብር በቀጣይ ኦሎምፒክ የተሻለ ውጤት እንዲመጣ ሁሉም በጋራ ሊረባረብ ይገባልም ብለዋል።
በውድድሩ ኢትዮጵያ በሰባት አይነት ስፖርቶች ተሳትፎ ማድረጓን ያነሱት የኦሎምፒክ ኮሚቴ ምክትል ዋና ጸሐፊ ገዛኸኝ ወልዴ ለውድድሩ ጠንካራ ዝግጅት መደረጉን አንስተዋል።
በውድድሩ ኢትዮጵያ ለመጀመሪያ ጊዜ በተሳተፈችበት የክብደት ማንሳት ውድድር ያስመዘገበችው ውጤት ማንኛውም ስፖርቶች ላይ ከተሠራ ውጤት ማምጣት እንደሚቻል ማሳያ ነው ብለዋል።
ኢትዮጵያ በአራተኛው የአፍሪካ ወጣቶች ኦሎምፒክ ጨዋታወች 8 ወርቅ፣ 9 ብር እና 16 የነሐስ በድምሩ በ33 ሜዳሊያ ውድድሩን አጠናቅቃለች።
ዘጋቢ፦ ቴዎድሮስ ኃይለኢየሱስ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here