ባሕር ዳር: ታኅሣሥ 14/2018 ዓ.ም (አሚኮ) በ35ኛው የአፍሪካ ዋንጫ ዛሬ አራት ጨዋታዎች ይደረጋል፡፡ ምድብ አምስት ላይ የሚገኙት አልጄሪያ እና ሱዳን ምሽት 12፡00 ላይ ይጫወታሉ።
ጨዋታው 22ሺህ ተመልካች በሚይዘው ሙላይ አል ሃሰን ስታዲየም ነው የሚከናዎነው።
ሁለቱ ሀገራት ከ2011 ወዲህ በስድስት ጨዋታዎች ተገናኝተው አልጀሪያ በሁለቱ ስታሸንፍ ሱዳን በአንድ ጨዋታ ድል አድርጋለች። በሦስት ጨዋታዎች ደግሞ አቻ ተለያይተዋል።
ሱዳን የአፍሪካን ዋንጫን ከመሠረቱ ሀገራት አንዷ ናት። እንደ አውሮፓ አቆጣጠር በ1959 እና በ1963 ሁለተኛ ደረጃን ይዛ ማጠናቀቋን ታሪክ ይዘክራል። በ1970 ደግሞ ዋንጫውን ወስዳለች።
የሱዳን ዋና አሰልጣኝ ክዌሲ አፒያህ በጨዋታው የሀገሪቱን ሰንደቅ አላማ ከፍ ለማድረግ እና በጦርነት እንዲሁም በረሃብ የጠቆረውን ታሪክ ወደ አብርኆት ዘመን ለመቀየር እንጫወታለን ብለዋል።
የአሰልጣኙን አስተያዬት ተከትሎ በዛሬው ጨዋታ በጦርነት እየተናጠች የምትገኘው ሱዳን በእግር ኳሱ ዘርፍ ከፍ ብላ ለመታየት ብርቱ ፉክክር ታደርጋለች ሲሉ ተንትነዋል።
አልጀሪያ በአፍሪካ ሀገራት የደረጃ ሰንጠረዥ አራተኛ ላይ ትገኛለች።
በርካታ ስመ ጥር ተጫዋቾቿ በአውሮፖ ፣ እስያ እና አፍሪካ ሀገራት በሚገኙ ተዋቂ ቡድኖች በፕሮፌሽናልነት በመጫወት ላይ ናቸው።
የሀገሪቱ ብሔራዊ ቡድን በአፍሪካን ዋንጫ እንደ አውሮፓ አቆጣጠር በ1990 እና በ2019 አሸንፏል።
አልጀሪያ እግር ኳሷ የደረሰበትን ከፍታ ለዓለም ኀብረተሰብ በማሳየት ገጽታዋን ለማድመቅ ትጫወታለች ሲል ዴይሊ ሜይል ስፖርት አስነብቧል።
በዚሁ ምድብ የሚገኙት ቡርኪና ፋሶ እና ኢኳቶሪያል ጊኒ ቀን 9፡00 ተኩል በስታዲ ሞሐመድ አምስተኛ ስታዲየም ይጫወታሉ።
ምድብ ስድስት ላይ ምሽት 2፡30 ኮትዲቯር (አይቮሪ ኮስት) እና ሞዛምቢክ በስታዲ ዴ ማራካሽ ስታዲየም የሚያደርጉት ጨዋታ ይጠበቃል።
በዚሁ ምድብ ካሜሩን እና ጋቦን ምሽት 5:00 ሰዓት ላይ በስታዲ ደ’ አጋዲር ጨዋታቸውን ያደርጋሉ።
ትናንት በተደረጉ ጨዋታዎች ቱኒዚያ ዑጋንዳን 3 ለ 1፣ ናይጄሪያ ታንዛኒያን 2 ለ 1 እንዲሁም ዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ ቤኒንን 1 ለ 0 በኾነ ውጤት ማሸነፋቸው ይታዎሳል።
በሙሉጌታ ሙጨ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!



