የቪላ ፓርኩ ግጥሚያ ተጠባቂ ነው።

0
4
ባሕር ዳር: ታኅሣሥ 12/2018 ዓ.ም (አሚኮ) በእንግሊዝ ፕሪምየር ሊግ አስቶን ቪላ ያለበትን ደረጃ ለማጠናከር ማንቸስተር ዩናይትድ ደግሞ ደረጃው ለማሻሻል ዛሬ ምሽት የሚያደርጉት ጨዋታ አጓጊ ኾኗል።
በሊጉ 17ኛ ሳምንት መርሐ ግብር ምሽት 1:30 አስቶን ቪላ በሜዳው ቪላ ፓርክ ማንቸስተር ዩናይትድን የሚገጥምበት ጨዋታ እስካሁን የመጣበትን የጥንካሬ ጉዞ ዛሬም ያስቀጥላል የሚለወን መልስ የሚሰጥ ነው።
አስቶን ቪላ በፕሪምየር ሊጉ ካደረጋቸው 16 ጨዋታዎች በ10 አሸንፏል። በሦሥቱ አቻ ወጥቶ እና በሦሥቱ ተሸንፎ 33 ነጥብ በመሰብሰብ እና ስምንት የግብ ክፍያ በመያዝ በደረጃ ሰንጠረዡ በሦሥተኛነት ተቀምጧል።
የዛሬውን ጨዋታ ካሸነፈም ነጥቡን 36 በማድረስ ባለበት ደረጃ ረግቶ የሚቀመጥ ይኾናል።
አሰልጣኝ ዑናይ ኢምሪ ዛሬ ፓኦ ቶሬስ፣ ታይሮን ሚንግስ እና ሮዝ ባርክሌይ በጉዳት የማይሰለፏቸው ተጫዋቾች መኾናቸው ደግሞ ጨዋታውን ፈታኝ ያደርግበታል ሲል ዴይሊ ሜይል ስፖርት አስነብቧል።
ማንቸስተር ዩናይትድ በበኩሉ ከ16 ጨዋታዎች በሰባት ጨዋታዎች አሸንፎ፣ በአምስቱ አቻ ተለያይቶ እና በአራት ጨዋታ ተሸንፎ እና አራት የግብ ክፍያ በመያዝ በ26 ነጥብ ሰባተኛ ደረጃን ይዟል።
ማንቸስተር ዩናይትድ ጨዋታውን ካሸነፈ ነጥቡን 29 በማድረስ ሊቨርፑልን በግብ ክፍያ በመብለጥ የአምስተኛ ደረጃን የሚረከበው ይኾናል።
የቀያይ ሰይጣኖች አሠልጣኝ ሩብን አሞሪም በአፍሪካ ዋንጫ ምክንያት ወሳኝ ተጫዋቾችን ሳይዝ እንደመጫወቱ በጨዋታው በእጅጉ ይፈተናል እየተባለ ነው።
በጉዳት ምክንያት ደግሞ ማቲያስ ዴሊት እና ሃሪ ማጓየርንም አያሰልፍም።
ሁለቱ ቡድኖች በታሪክ በ200 ጨዋታዎች ተገናኝተዋል። ማንቸስተር ዩናይትድ 107 ጨዋታዎችን በማሸነፍ የበላይ ነው።
አስቶን ቪላ ደግሞ በ51 ጨዋታዎች ድል ነስቷል። በ42 ጨዋታዎች አቻ ተለያይተዋል ሲል ስፖርት ሜል አስነብቧል።
ዛሬስ? ምሽት 1:30 ላይ ከ43 ሺህ በላይ ተመልካች በሚይዘው ቪላ ፓርክ ስታዲየም የሚጀምረው ጨዋታ ምላሹን ይሰጣል።
በሙሉጌታ ሙጨ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here