ባሕር ዳር: ታኅሣሥ 12/2018 ዓ.ም (አሚኮ) የ2025ቱ የአፍሪካ ዋንጫ በሞሮኮ አስተናጋጅነት ዛሬ ይጀምራል። ሞሮኮ ኮሞርስን የምትገጥምበት ጨዋታም የውድድሩ የመክፈቻ ጨዋታ ነው።
ስለ አፍሪካ ዋንጫው ከታሪክ በትቂቱ


አዘጋጇ ሞሮኮ ዋንጫውን ለማንሳት ቅድመ ግምት በማግኘት ቁጥር አንድ ላይ መቀመጧን አልጀዚራ አስነብቧል። ኮትዲቫር፣ ሰኔጋል እና ግብጽም ዋንጫ የማንሳት ቅድመ ግምት ያገኙ ሀገራት ናቸው።

ኮትዲቯር የ2023ቱ የአፍሪካ ዋንጫ ባለቤት ናት

ሞሮኮ ለውድድሩ በስድስት ከተሞች የሚገኙ ዘጠኝ ስታዲየሞችን አዘጋጅታለች። ይህም በአፍሪካ ዋንጫ ታሪክ ብዙ ሜዳዎች ጨዋታ የሚያስተናግዱበት የአፍሪካ ዋንጫ ያደርገዋል።

ካፍ የ2025ቱን የአፍሪካ ዋንጫ እንድታዘጋጅ መጀመሪያ ለጊኒ እድል ሰጥቶ የነበረ ቢኾን በኋላ ላይ በሀገሪቱ የአዘጋጅነት ላይ እምነት በማጣቱ እድሉን ነጥቆ ለሞሮኮ ሰጥቷል።

ግብጽ የአፍሪካ ዋንጫን ሰባት ጊዜ በማንሳት ቀዳሚዋ ሀገር ናት።

ሞሮኮ የአፍሪካ ዋንጫን ስታዘጋጅ ይህ ሁለተኛዋ ሲኾን ከዚህ በፊት እ.ኤ.አ 1988 አዘጋጅታ ነበር።

አዘጋጇ ሞሮኮ የአፍሪካ ዋንጫን ያሸነፈችው በታሪክ አንድ ጊዜ ሲሆን ጊዜው እንደአውሮፓውያን አቆጣጠር 1976 ኢትዮጵያ ባዘጋጀችው ድግስ ነበር።

የዘንድሮውን ዋንጫ የሚያነሳ ሀገር 7 ሚሊዮን ዶላር የሚሸለም ሲኾን ሁለተኛ ደረጃን ይዞ የሚያጠናቅቀው ደግሞ 4 ሚሊዮን የአሜሪካን ዶላር ይበረከትለታል።

እነዚህን ሽልማቶች ጨምሮ ካፍ 32 ሚሊዮን ዶላር ለዚህ ውድድር ለሽልማት አዘጋጅቷል።

የአፍሪካ ዋንጫ በሦስት ሀገራት የተጀመረ ሲሆን አሁን ላይ 24 ሀገራት የማጣሪያ ጨዋታቸውን አልፈው ሞሮኮ ላይ ለመድመቅ ውድድሩን እየተጠባበቁ ነው።