ስለሞሮኮ እና ኮሞሮስን ብሔራዊ ቡድኖች በጥቂቱ፦

0
4
ባሕር ዳር: ታኅሣሥ 12/2018 ዓ.ም (አሚኮ) 35ኛው የአፍሪካ እግር ኳስ ዋንጫ ዛሬ ሞሮኮ ራባት ከተማ በሚገኘው እና 68 ሺህ 700 ተመልካች በሚይዘው ልዑል ሙላይ አብደላህ ስታዲየም በይፋ ይጀመራል፡፡
የመክፈቻ ጨዋታው ምድብ አንድ ላይ በተደለደሉት ሞሮኮ እና ኮሞሮስ መካከል ምሽት 4 ሰዓት ይደረጋል፡፡ጨዋታው በመላው ዓለም በ”ቻናል 4″ ኔትወርክ ላይ ይተላለፋል።
የሞሮኮ እና ኮሞሮስን የእግር ኳስ ጨዋታ ግንኙነት ስንቃኝ ሁለቱ ቡድኖች በታሪክ ከዚህ በፊት አራት ጊዜ ተገናኝተዋል፡፡
የመጀመሪያ ግጥሚያቸውንም በ2019 ለተደረገው የአፍሪካ ዋንጫ ተጫውተው ሞሮኮ 1ለ0 አሸንፋለች፡፡ የመልስ ጨዋታው ደግሞ ኮሞሮስ ላይ ተካሄዶ 2ለ2 በኾነ ውጤት ተጠናቋል።
በጠቅላላው ሁለቱ ቡድኖች በታሪክ በነበራቸው የእርስ በርስ ጨዋታ ሞሮኮ በሦሥቱም አሸንፋለች፡፡ አንድ ጨዋታ ደግሞ በአቻ ውጤት ተጠናቋል፡፡
ሞሮኮ በፍሪካ እግር ኳስ የደረጃ ሰንጠረዥ ቀዳሚዋ ሀገር ናት፡፡ በፊፋ የእግር ኳስ ደረጃ ደግሞ 11ኛ ላይ ትገኛለች፡፡
የሞሮኮ ብሔራዊ የእግር ኳስ ቡድን “የአትላስ አናብስት” ቅጽል ስሙ ነው፡፡
ብሔራዊ ቡድኑ በታሪኩ የአፍሪካን ዋንጫ ማሸነፍ የቻለው እንደ አውሮፓ አቆጣጠር በ1976 ኢትዮጵያ ባዘጋጀችው ውድድር ላይ ብቻ ነው፡፡ በ2004 በሁለተኛነት በማጠናቀቅ የብር ሜዳሊያ አጥልቋል፡፡
ዘ ስፖርትስ እንዳስነበበው ሞሮኮ ብቃት ያለው ብሔራዊ የእግር ኳስ ቡድን ገንብታለች፡፡ የሞሮኮ የእግር ኳስ ቡድን የሀገሪቱ ብሔራዊ መለያ ነው (ብራንድ) እስከ መባልም ደርሷል፡፡
የአትላስ አናብስት ለመለያቸው የማይደክሙ እና በዓለም አቀፍ ደረጃ ላይ ከፍተኛ ተጽዕኖ ፈጣሪዎች ናቸው፡፡ መገለጫቸው ደግሞ በሜዳቸው ላይ ያደረጉትን 17 የቅርብ ጨዋታዎች አሸንፈዋልና ነው፡፡
ብሔራዊ ቡድኑ ቴክኒካዊ እና ታክቲካዊ ዲሲፕሊንን እና ዓለም አቀፍ ልምድን በማጣመር በአፍሪካ ውስጥ ካሉት እጅግ የተሟሉ ቡድኖች አንዱ መኾኑን ቢቢሲ ስፖርት አስነብቧል፡፡
በኳታር በተካሄደው የፊፋ ዓለም ዋንጫ ላይ የሞሮኮ ብሔራዊ ቡድን ባሳየው ብቃት ግማሽ ፍፃሜ መድረሱ የጥንካሬው መገለጫ ነው፡፡
የቡድኑ ዋና አሠልጣኝ ዋሊድ ሪጉራጊ “እግር ኳስ የማሸነፍ ዋስትና የለውም፡፡ ነገር ግን እኛ ወኔ ያላቸውን ወጣት ተጫዋቾችን ልምድ ካላቸው ተጫዋቾች ጋር አዋሕደን ነው የቀረብነው፤ በመኾኑም የማሸነፍ ብቃት እና እድላችን ከፍተኛ ነው ብለዋል።
የተዘጋጀነው ኮሞሮስን ለማሸነፍ ብቻ ሳይኾን በደጋፊዎቻችን ድጋፍ ታግዘን የአፍሪካ ሻምፒዮን ለመኾን ነው የምንጫወተው” ብለዋል፡፡
ወደ ኮሞሮስ ስንሻገር እንደ አውሮፓ አቆጣጠር 2025 በተደረገ የሕዝብ ቆጠራ የኮሞሮስ ሕዝብ ከ900 ሺህ አይበልጥም፡፡ ሀገሪቱ የአፍሪካ እግር ኳስ ኮንፌዴሬሽን አባል የኾነችው እንደ አውሮፓ አቆጣጠር በ2004 ነው፡፡
ብሔራዊ ቡድኗ “ሌስ ኮሌካንቴስ” ቅጽል ስሙ ነው፤ ዓሣዎቹ እንደማለት ነው። በፊፋ የእግር ኳስ ደረጃ ደግሞ 108ኛ ላይ ይገኛል፡፡
በአፍሪካ ዋንጫ በ2021 ለመጀመሪያ ጊዜ በመሳተፍም ጥሎ ማለፍ ድረስ መጓዝ ችላለች፡፡ ይህም እግር ኳሷ ምን ያህል በፍጥነት እያደገ እንደመጣ ተነጋሪ ነው፡፡
በ35ኛው የአፍሪካ ዋንጫ ለሁለተኛ ጊዜ የምትሳተፈው ኮሞሮስ በእድል ሳይኾን በአሳማኝ ብቃት ለውድድሩ መድረሷን በርካቶችን አስማምቷል፡፡
ይህም እንደ ኢትዮጵያ ላሉ ከ100 ሚሊዮን በላይ ሕዝብ ላላቸው ሀገራት አስተማሪነቱ ከፍተኛ ነው፡፡
የኮሞሮስ ብሔራዊ ቡድን አሠልጣኝ ስቴፋኖ ኩሲን የመክፈቻ ጨዋታን ያውም በአዘጋጁ ሀገር ሜዳ ማድረግ ከባድ ነው ብለዋል፡፡ ይሁንና በውድድሩ በውጤት የታጀበ አስገራሚ ቡድን መኾን እንፈልጋለን፤ ለዚህም ተዘጋጅተናል” ብለዋል፡፡
አሠልጣኙ አክለውም “ተጫዋቾቼ የሀገራቸውን ሰንደቅ ዓላማ በልባቸው ይዘዋል፤ የሕዝቡን ስሜት ተረድተዋል፤ እናም ለሀገር ክብር ወኔ በዲሲፕሊን እና በከፍተኛ ትኩረት ስለሚጫወቱ እናሸንፋለን” ነው ያሉት፡፡
ሁሉም ተጫዋቾች በጥሩ የአካል ብቃት እና ሥነ ልቦና ላይ እንደሚገኙም አሠልጣኙ ተናግረዋል፡፡
በሞሮኮ እና ኮሞሮስ መካከል የሚደረገውን የአፍሪካ ዋንጫ የመክፈቻ ጨዋታም የዴሞክራቲክ ኮንጎ ዳኛ ዣን ዣኩስ ንዳላ እንደሚመሩት የአፍሪካ እግር ኳስ ኮንፌደሬሽን (ካፍ) አሳውቋል፡፡
ረዳት ዳኞች፣ አራተኛው ዳኛ እና የጨዋታው ኮሚሽነርም ከዴሞክራቲክ ኮንጎ የተመረጡ ኾነዋል፡፡ የቫር ዳኞች ደግሞ ከሞሪታኒያ ኾነው ተመድበዋል ሲል የአፍሪካ እግር ኳስ ኮንፌዴሬሽን (ካፍ) አስነብቧል።
በሙሉጌታ ሙጨ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here