ተደራሽነቱ የሰፋው የአፍሪካ ዋንጫ!

0
8
ባሕር ዳር: ታኅሣሥ 09/2018 ዓ.ም (አሚኮ) 35ኛው የአፍሪካ ዋንጫ በመጭው እሁድ ራባት ከተማ በሚገኘው እና 68 ሺህ 700 ተመልካች በሚይዘው ልዑል ሙላይ አብደላህ ስታዲየም ሞሮኮ እና ኮሞሮስ በሚያደርጉት ጨዋታ ይጀመራል፡፡
በአፍሪካ 24 ሀገራትም ተሳታፊ ይኾኑበታል፡፡ ጨዋታው በስድስት ከተሞች በሚገኙ ዘጠኝ ዘመናዊ ስታዲየሞች ይካሄዳል፡፡
የአፍሪካ እግር ኳስ ኮንፌዴሬሽን (ካፍ) የጨዋታውን ተደራሽነት ለማስፋት መቀመጫቸውን አውሮፓ ካደረጉ ከ20 የመገናኛ ተቋማት ጋር በአጋርነት (በብሮድካስት ሽርክና) ለመሥራት መስማማቱን አስታውቋል።
በስምምነቱ ላይ እንደተገለጸው የቴሌቪዥን ጣቢያዎቹ ከ30 በላይ በሚኾኑ የአውሮፓ ሀገራት ጨዋታዎችን በቀጥታ ያሥተላልፋሉ፡፡
ይህም በመላው አውሮፓ የሚገኙ በሚሊዮን የሚቆጠሩ የእግር ኳስ ቤተሰቦች እንዲሁም አፍሪካውያን ዲያስፖራዎች ጨዋታውን በቀጥታ እንዲከታተሉ ያስችላቸዋል ነው የተባለው፡፡
በስምምነቱ ከተካተቱት መካከል ዩናይትድ ኪንግደም ውስጥ ያለው “ቻናል 4” ሁሉም ጨዋታዎች ለስርጭት እንደሚያበቃ ተገልጿል፡፡ በስፔን የሚገኘው ሞቪስታርም እንዲሁ፡፡
በግሪክ፣ ኖርዌይ፣ ጣሊያን፣ ጀርመን፣ ኦስትሪያ፣ ስዊዘርላንድ፣ ክሮሽያ፣ ስሎቫኒያ፣ ቡልጋሪያ፣ ኮሶቮ፣ ቆጵሮስ፣ ተርክዬ፣ ሩሲያ፣ ፖርቱጋል፣ ፈረንሳይ፣ እስራኤል፣ ፖላንድ፣ ዩክሬን፣ ካዛኪስታን እና ኔዘርላንድስ የሚገኙ የመገናኛ ተቋማትም ከካፍ ጋር በአጋርነት የአፍሪካ ዋንጫን የቀጥታ ሽፋንን ለመስጠት ከተስማሙት ተቋማት መካከል ይገኙበታል ሲል ያስነበበው ካፍ ኦንላይን ኒውስ ነው፡፡
ካፍ ስምምነቱን አስመልክቶ እንዳተተው ጨዋታዎች የሚተላለፉበት አድማስ በሰፋ ቁጥር የአፍሪካ እግር ኳስን ጥንካሬ ይበልጥ ጎልቶ ይታያል፡፡
ምርጥ ተሰጥኦ ያላቸው ተጫዋቾችም እንዲታዩ ያደርጋል፤ የስፖርት ቱሪዝም ያነቃቃል፤ ገበያንም ይስባል ብሏል፡፡ በጠቅላላው የዓለም ማኅበረሰብ ለአፍሪካውያን ያለውን አዎንታዊ ምልከታ አጉልቶ እንዲመለከት የነበረበትን ብዥታም እንዲያጠራ ያስችለዋል ነው ያለው፡፡
ይህ በዚህ እንዳለ ለአፍሪካውያን እና ለቀሪው ዓለም ጨዋታዎችን በቀጥታ ለማድረስ ከካፍ ጋር ስምምነት የገባው ኒው ወርልድ ቲቪ ነው፡፡
የቴሌቪዥን ጣቢያውም ከ52 ጨዋታዎች 32ቱን ብቻ ለአፍሪካውያን በነጻ ለማስተላላፍ ከካፍ ጋር ስምምነት ላይ የደረሰ መኾኑ ቅሬታ አስነስቷል፡፡
በሙሉጌታ ሙጨ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here