ባሕር ዳር: ታኅሣሥ 06/2018 ዓ.ም (አሚኮ) በእንግሊዝ ፕሪምየር ሊግ 16ኛ ሳምንት መርሐ ግብር ዛሬ ማንቸስተር ዩናይትድ ከ74 ሺህ በላይ ተመልካች በሚይዘው ኦልድ ትራፎርድ ስታዲየም ምሽት 5:00 ላይ ከቦርንማውዝን ጋር ይጫወታል።
ማንቸስተር ዩናይትድ በሊጉ 15 ጨዋታዎችን አድርጎ በሰባት ጨዋታዎች አሸንፏል።
በአራት ጨዋታዎች አቻ ተለያይቶ በአራቱ ደግሞ ተሸንፎ 25 ነጥብ በመሰብሰብ ስምንተኛ ደረጃ ላይ ይገኛል። ቀያይ ሠይጣኖች የዛሬውን ጨዋታ ካሸነፉ አምስተኛ ላይ መቀመጥ ያስችላቸዋል።
አሠልጣኝ ሩበን አሞሪም የቀደምት ስመ ጥር ተጫዋቾች በቡድኑ ውጤት ማጣት ላይ ስለሚሰጡት ትችት ተጠይቀው” የሚጠበቅ እና የተለመደ ነው” ብለዋል።
አሠልጣኙ አያይዘውም ቡድኑ ውጤት ያጣበትን ምክንያት በግምገማ መለየቱን ተናግረዋል። እናም ዛሬ በሜዳቸው የተሻለ ለመጫወት መዘጋጀታቸውን ነው የጠቆሙት።
በማንቸስተር ዩናይትድ በኩል ሃሪ ማጉዌየር በጉዳት ምክንያት አይሰለፍም ተብሏል። ቤንጃሚን ሼሽኮም የመሰለፉ ነገር ገና እንዳልተወሰነ አሠልጣኝ ሩበን አሞሪም ፍንጭ ሰጥተዋል።
ቦርንማውዝ ከ15 ጨዋታዎች በአምስቱ አሸንፎ፣ በአምስቱ አቻ ተለያይቶ፣ በአምስቱ ተሸንፎ፣ በሦስት የግብ ዕዳ 20 ነጥብ በመያዝ 15ኛ ደረጃ ላይ ተቀምጧል።
ዛሬ ማንቸስተር ዩናይትድን ካሸነፈ 11ኛ ደረጃ ላይ መቀመጥ ያስችለዋል። ሁለቱ ቡድኖች ከ2015 ወዲህ በ17 ጨዋታዎች ተገናኝተዋል።
ቀያይ ሰይጣኖች በ10 ጨዋታዎች አሸንፏል። ከዚህ ውስጥ ደግሞ ዘጠኙ ድል በኦልድ ትራፎርድ ስታዲየም የተገኘ ነው።
ቦርንማውዝ በአራት ጨዋታዎች ሲያሸንፍ ሁለቱ ድል የተመዘገበው በኦልድ ትራፎርድ ስታዲየም ነው። በሦስት ጨዋታዎች ደግሞ አቻ ተለያይተዋል።
የቦርንማውዝ አሠልጣኝ አንዶኒ ኢራኦላ ለጨዋታው ልዩ ሥራ ማከናወናቸውን እና የተለየ አሰላለፍን እንደሚጠቀሙ ተናግረዋል።
ሊጉን አርሰናል በ36 ነጥብ ይመረዋል፤ ማንቸስተር ሲቲ እና አስቶን ቪላ ሁለተኛ እና ሦስተኛ ደረጃን ይዘው ይገኛሉ።
ዌስት ሃም ዩናይትድ፣ በርንሌይ እና ዎልቨርሃምፕተን ወራጅ ቀጣና ላይ ተቀምጠዋል።
በሙሉጌታ ሙጨ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!



