ባሕር ዳር: ታኅሣሥ 05/2018 ዓ.ም (አሚኮ) የኢትዮጵያ ዋንጫ ሦስተኛ ዙር ጨዋታ ዛሬም ቀጥሎ ይውላል።
የአማራ ክልል ተወካዩ ደብረ ብርሃን ከተማ ከቤንች ማጂ ቡና ጋር ቀን 7፡00 ሰዓት ላይ በአዲስ አበባ ስታዲየም ይጫወታል።
ደብረ ብርሃን ከተማ በሁለተኛው ዙር የኢትዮጵያ ዋንጫ ጨዋታ አዲስ ከተማ ክፍለ ከተማን በመለያ ምት 7 ለ 6 አሸንፎ ነው ለዚህ ጨዋታ የደረሰው። በ2018 ዓ.ም በከፍተኛ ሊግ ምድብ “ለ” ላይ የተደለደለው ደብረ ብርሃን ከተማ በሊጉ አምስት ጨዋታዎችን አድርጓል።
አምስት ነጥብ በመያዝም ሰባተኛ ደረጃ ላይ ተቀምጧል። ቡድኑ ከጨዋታ ጨዋታ ከፍተኛ መሻሻልን በማድረግ ነው ከነበረበት 11ኛ ደረጃ ወደ ሰባተኛ ደረጃ ከፍ ያለው።
ተጋጣሚው ቤንች ማጂ ቡና ለሦስተኛው ዙር ኢትዮጵያ ዋንጫ የበቃው ጋሞ ጨንቻን አሸንፎ ነው።
በከፍተኛ ሊግ ምድብ “ሀ” ላይ እየተወዳደረ የሚገኘው ቤንች ማጂ ቡና በበኩሉ በሊጉ ስድስት ጨዋታዎችን አድርጓል። ሰባት ነጥብ በመያዝም ስድስተኛ ላይ ተቀምጧል ሲል የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን በድረ ገጹ አስነብቧል።
ከደብረ ብርሃን ከተማ እና ከቤንች ማጂ ቡና አሸናፊው ቡድን ለኢትዮጵያ ዋንጫ ሩብ ፍጻሜ የሚደርስ በመኾኑ ጨዋታው ከፍተኛ ፉክክር ይደረግበታል ተብሎ ተጠብቋል።
ትናንት በኢትዮጵያ ዋንጫ ሩብ ፍጻሜ ለመድረስ በከፍተኛ ሊግ ከሚሳተፈው ቦዲቲ ከተማ ጋር የተጫወተው የፕሪሚየር ሊጉ ተፎካካሪ ባሕር ዳር ከተማ በመደበኛው የጨዋታ ሰዓት አንድ አቻ በመለያየቱ በፍጹም ቅጣት ምት 6 ለ 5 ተሸንፎ ከውድድሩ ተሰናብቷል።
አማራ ክልልን በኢትዮጵያ ዋንጫ ወክሎ የሚጫወተው ደብረ ብርሃን ከተማ ዛሬ ድል ከቀናው ሩብ ፍጻሜውን ይቀላቀላል።
በሙሉጌታ ሙጨ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!



