የአፍሪካ ዋንጫ ስጋት የፈጠረባቸው የፕሪምየር ሊጉ ክለቦች።

0
9

ባሕር ዳር: ታኅሣሥ 02/2018 ዓ.ም (አሚኮ) በሞሮኮ አስተናጋጅነት የሚካሄደው የአፍሪካ ዋንጫ ከታኅሣሥ 12/2018 ዓ.ም ጀምሮ በሞሮኮ የተለያዩ ስታዲየሞች ይካሄዳል፡፡ በዚህ ውድድር በርካታ የአውሮፓ ሀገራት አፍሪካዊ የእግር ኳስ ኮከቦችን ወደ ሞሮኮ ይሸኛሉ፡፡

ሞሮኮ በምታስተናግደው የአፍሪካ ዋንጫ 17 የእንግሊዝ ፕሪምየር ሊግ ክለቦች ተጨዋቾቻቸውን ያጣሉ፡፡ የማይገመቱ ውጤቶች እየተመዘገቡበት ከሳምንት ወደ ሳምንት አጓጊነቱን የቀጠለው የእንግሊዝ ፕሪምየር ሊግ እንደ ማንቸስተር ዩናይትድ ያሉ ክለቦች ይበልጥ ተጎጂ ሊሆኑ ይችላሉ የሚሉ መረጃዎችን ቢቢሲ ስፖርት አጋርቷል፡፡

በዘንድሮው የአፍሪካ ዋንጫ ምንም ዓይነት ተጨዋች ወደ ሞሮኮ የማይልኩት አርሰናል፣ ቼልሲ እና ሊድስ ዩናይትድ ናቸው፡፡ በአንጻሩ ደግሞ ሰንደርላንድ እና ዎልቭስ ብዙ ተጨዋቾችን ለአፍሪካ ዋንጫ በመላክ የበለጠ ተጎጂዎች እንዳይኾኑ ተሠግቷል፡፡

ማንቸስተር ዩናይትዶች ሦስት ወሳኝ ተጨዋቾቻቸውን ለአፍሪካ ዋንጫ በመሸኘት ፈተናዎች ከሚበዙባቸው ክለቦች ውስጥ በግንባር ቀደምትነት ተጠቃሾች ኾነዋል፡፡ ካሜሮናዊውን የመሥመር አጥቂ ብሪያን ምቤሞ፣ አይቮሪኮስታዊውን አማድ ዲያሎ እና ተከላካዩን ሞሮኳዊ ማዝራዊን ማጣታቸው በእጅጉ የሚፈተኑበት ጊዜ ከፊታቸው እንዳለ ጠቋሚ ነው ተብሏል፡፡

ሰንደርላንድ ሰባት ያህል ተጨዋቾችን ወደ ሞሮኮ በመሸኘት ባደጉበት ዓመት እያሳዩ በሚገኙት ምርጥ እንቅስቃሴ ላይ ቀይ መብራት የሚበራባቸው ይመስላል፡፡

ቼምሰዲን ታልቢን ለሞሮኮ፣ ሀቢብ ዲያራን ለሴኔጋል፣ ሬይኒልዶን ለሞዛምቢክ፣ ሲሞን አዲንግራን ለአይቮሪኮስት፣ በርትራንድ ትራኦሬን ለቡርኪናፋሶ፣ አርቱር ማሱዋኩ እና ዋህ ሳዲክን ደግሞ ለዲሞክራቲክ ኮንጎ ይሸኛሉ፡፡

በፕሪምየር ሊጉ የመጨረሻውን ደረጃ የያዙት እና የመውረድ ሥጋት በከፍተኛ ሁኔታ የተደቀነባቸው ዎልቭሶች አምስት ተጨዋቾችን ወደ አፍሪካ ዋንጫ ሸኝተው የወራጅነት ትኬታቸውን ከወዲሁ የሚቆርጡ ይመስላሉ፡፡

ብሬንትፎርዶች የቡርኪናፋሶውን አጥቂ ዳንጎ ኳታራን ያጣሉ፡፡ ብሬንትፎርዶች በክረምቱ ዝውውር ከ42 ሚሊዮን ዩሮ በላይ ያወጡበትን አጥቂ ማጣታቸው በቀጣይ ውጤታቸው ላይ ተጽዕኖ ያሳድርባቸዋል ተብሎ ተሠግቷል፡፡

ብራይተኖች ወሳኝ የተከላካይ አማካይ ተጨዋቻቸውን ካሜሮናዊውን ካርሎስ ባሌባን ለአሕጉራዊው ውድድር የሚሸኙት ይኾናል፡፡

በርንሌዮች ሦስት ተጨዋቾቻቸውን ለአፍሪካ ዋንጫ በመላክ ላለመውረድ በሚያደርጉት ፍልሚያ ላይ ሌላ ችግር ይፈጠርባቸዋል ተብሏል፡፡ አክሲል ቱአንዜቢን ለዴሞክራቲክ ኮንጎ፣ አጥቂው ሊሌ ፎስተርን ለደቡብ አፍሪካ እና የአጥቂ አማካዩን ሃኒባልን ለቱኒዚያ ይሸኛሉ፡፡

ክሪስታል ፓላሶች ሴኔጋላዊውን ኢስማኤል ሳር እና ሞሮኳዊውን ቻዲ ሪያድ ለአፍሪካ ዋንጫ የሚልኩ ሲኾን ኤቨርተኖችም ወሳኝ ተጨዋቾቻቸውን ሊማን ኒዳዬን እና ኢዲሪሳ ጉዬን ለሴኔጋል ብሔራዊ ቡድን ይሸኟቸዋል፡፡

ፉልሃሞች እስካሁን ባሉት ሁሉም የፕሪምየር ሊጉ ጨዋታዎች ያሰለፏቸውን ናይጄሪያዊዎቹን አሌክሲ ኢዎቢን እና ካልቪን ባሲን ወደ ሞሮኮ ሸኝተው ፈተናዎችን የሚጋፈጡ ይኾናል፡፡

ማንቸስተር ሲቲዎችም ሁለት ወሳኝ ተጨዋቾቻቸውን ማለትም ግብጻዊውን አጥቂ ኦማር ማርሙሽን እና አልጄሪያዊውን የግራ መሥመር ተከላካይ ራይን ኤይት ኑሪን ወደ ሞሮኮ በመሸኘት የቡድን ጥልቀታቸውን ይቀንሳሉ፡፡

ሊቨርፑሎች በአፍሪካ ዋንጫ ምክንያት የሚያጡት አንድ ተጨዋች ብቻ ቢኾንም ያው አንድ ተጨዋች ግን ብዙ ትርጉሞች ያሉት ተጨዋች ነው፡፡

ግብጻዊው ሞሀመድ ሳላህ ለአምና የፕሪሚየር ሊጉ ሻምፒዮኖች ብዙ ነገራቸው ነበር፤ ዘንድሮ ግን በተከታታይ ጨዋታዎች ተጠባባቂ ከመኾኑም ባሻገር በአውሮፓ ሻምፒዮንስ ሊግ ኢንተር ሚላንን ለመግጠም ወደ ጣሊያን ከተጓዘው የቡድን ሥብሥብ ውጪም ተደርጓል፡፡

በሊቨርፑል ቤት ተገፍቻለሁ የሚለው ሞሀመድ ሳላህ በቅርቡ ከክለቡና ከአሠልጣኙ ጋር የገጠመውን እሰጣቸዋለሁ አገባ ሳይቋጭ ወደ ሞሮኮ ያቀናል፡፡

በቀዮቹ ቤት ቋሚ አሠላለፍን የተነፈገው የፈርዖኖቹ አጥቂ ከአፍሪካ ዋንጫ ሲመለስ ስለሚኖረው ዕጣ ፈንታም አሁን ላይ ኾኖ መተንበይ አስቸጋሪ ኾኗል፡፡

አስቶን ቪላ እና በርንማውዝም አንድ አንድ ተጨዋቾችን ብቻ ለአፍሪካ ዋንጫ የሚሸኙ የእንግሊዝ ፕሪምየር ሊግ ክለቦች ናቸው፡፡

የአፍሪካ ዋንጫ መርሐ ግብር የአውሮፓ ክለቦች ወሳኝ ጨዋታዎችን በሚያካሂዱበት ወቅት ላይ መከናወኑ የብዙ አሠልጣኞችን ትችት እያስተናገደ አኹንም ድረስ ቀጥሏል፡፡

ለብዙ የአውሮፓ ክለቦች የውጤት ማጣት ሥጋት የደቀነው የአፍሪካ ዋንጫ በሞሮኮ አስተናጋጅነት ከታሕሳስ 12 እስከ ጥር 10 የሚካሄድ ይኾናል፡፡

ዘጋቢ፡- እሱባለው ይርጋ

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here