ወልቭስ ወይስ ማንቸስተር ዩናይትድ?

0
31

ባሕር ዳር: ኅዳር 29/2018 ዓ.ም (አሚኮ) በእንግሊዝ ፕሪሚየር ሊግ 15ኛ ሳምንት መርሐ ግብር ዛሬ ወልቭስ በሜዳው ከማንቸስተር ዩናይትድ ጋር ይጫወታል።

ወልቭስ ባለፈው ዓመት በማንቸስተር ዩናይትድ ያለመሸነፍ ታሪኩን ለመድገም ማንቸስተር ዩናይትድ ደግሞ ደረጃውን ከፍ ለማድረግ ብርቱ ፉክክር ያደርጋሉ ተብሎ ተጠብቋል።

ወልቭስ እስካሁን 14 ጨዋታዎችን ቢያደርግም በሁለት ጨዋታዎች አቻ ከመለያዬት ያለፈ አንድም ጨዋታ አላሸነፈም። ሁለት ነጥብ በመያዝም በሊጉ የደረጃ ሰንጠረዥ 20ኛ ላይ ይገኛል።

ወልቭስ ባለፈው የውድድር ዓመት ማንቸስተር ዩናይትድን በሜዳው እና ከሜዳው ውጭ በማሸነፍ ልዩ ታሪክ አስመዝግቧል። በዚህ እሳቤ መሠረትም በዛሬው ጨዋታ ማንቸስተር ዩናይትድን ይፈትነዋል የሚሉ በርካቶች ናቸው።

የወልቭስ አሠልጣኝ ሮብ ዑድዋርድስ “እንዴት ማሸነፍ እንደምንችል ከተጨዋቾች ጋር በመነጋገር ተግባብተናል ነው ያሉት።

በዘንድሮው ጨዋታ ቡድኑ ወጥ አቋም ባለመያዙ የተሸነፈበትን መንገድ ዛሬ ላለመድገም እንጫወታለንም በማለት ቡድኑ ባለፈው ዓመት በማንቸስተር ያልተሸነፈበትን ታሪክ ለመድገም እንደሚጫወቱ ተናግረዋል።

ማንቸስተር ዩናይትድ በሊጉ ካደረጋቸው 14 ጨዋታዎች በስድስት ጨዋታዎች አሸንፎ፣ በአራቱ አቻ ተለያይቶ እና በአራቱ ተሸንፎ በ22 ነጥብ 12ኛ ደረጃ ላይ ይገኛል።

ቡድኑ የዛሬውን ጨዋታ ካሸነፈ ነጥቡን 25 በማድረስ ስድስት ደረጃዎችን በማሻሻል ስድስተኛ ላይ ለመቀመጥ ያስችለዋል።

አሠልጣኝ ሩብን አሞሪም “በጨዋታው ማሸነፍ ብቻ ነው የምፈልገው” በማለት መዘጋጀታቸውን ፍንጭ ሰጥተዋል።

በማንቸስተር ዩናይትድ በኩል ቤንጃሚን ሼሽኮ እና ሃሪ ማጓየር እንደማይሰለፉ የሚጠቁሙ መረጃዎች ወጥተዋል።

ሁለቱ በድኖች እንደ አውሮፓውያኑ አቆጣጠር ከ2003 ጀምሮ ባደረጓቸው 28 ጨዋታዎች ማንቸስተር ዩናይትድ በ17 ጨዋታዎች በማሸነፍ የበላይ ነው።

በአንጻሩ ወልቭስ ያሸነፈው በሰባት ጨዋታዎች ብቻ ነው። በአራት ጨዋታዎች ደግሞ አቻ መለያየታቸውን ኤፍ ሲ ቴብልስ ዶት ኮም አስነብቧል።

ጨዋታው ምሽት 5፡00 ሰዓት ላይ ይደረጋል።

ሊጉን አርሰናል ማንቸስተር ሲቲን በማስከተል ሲመራው አስቶን ቪላ በሦስተኛነት ይከተላል።

ዌስትሃም ዩናይትድ፣ በርንሌይ እና ወልቭስ ወራጅ ቀጣና ላይ ይገኛሉ።

በሙሉጌታ ሙጨ

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here