ባሕር ዳር: ኅዳር 28/2018 ዓ.ም (አሚኮ) የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ዘጠነኛ ሳምንት ዛሬ በሚካሄዱ አራት ጨዋታዎች ይጠናቀቃል።
ፋሲል ከነማ ዛሬ ከመቀለ 70 እንደርታ ጋር 10፡00 አዲስ አበባ ላይ በሊጉ ተፎካካሪነቱን የሚያጠናክርበትን ጨዋታ ነው የሚያካሂደው። ፋሲል ከነማ ባለፉት ካደረጋቸው ስምንት ያህል ጨዋታዎች 16 ነጥብ ሰብስቦ ሁለተኛ ደረጃ ላይ ነው የተቀመጠው።
ዛሬ በሚያካሄደው ጨዋታ ደግሞ ሦስት ነጥብ ማግኘት ከቻለ በ19 ነጥብ ከሊጉ መሪ ሲዳማ ቡና በአንድ ነጥብ ዝቅ ብሎ ፉክክሩን ይበልጥ ጠንካራ እንዲኾን ያደርጋል።
ፋሲል ከነማ ባለፈው ስምንተኛ ሳምንት ጨዋታ ከወላይታ ዲቻ ጋር ያደረገውን ጨዋታ በአንድ አቻ ውጤት ነጥብ ተጋርቶ ነው የወጣው። ቡድኑ ታዲያ በዛሬው ጨዋታ ወደ አሸናፊነት ለመመለስ ነው ጨዋታውን የሚያደርገው።
ተጋጣሚው መቀለ 70 እንደርታ ደግሞ በሊጉ ስምንት ጨዋታ አድርጎ በ3 ነጥብ በደረጃ ሠንጠረዡ ግርጌ ነው የተቀመጠው።
ቡድኑ በስምንተኛው የሊጉ ሳምንት ጨዋታም በወልዋሎ አዲግራት ዩኒቨርሲቲ 1ለ0 ተሸንፎ ወደ ወራጅ ቀጣና እየተንደረደረ ያለ ክለብ ነው።
ፋሲል ከነማ ይህኛውን ጨዋታ የማሸነፍ ቅድመ ግምት ተሰጥቶታል።
በሊጉ ሌሎች ጨዋታዎችም ሲካሄዱ ሀዋሳ ከተማ ከመቻል በአዲስ አበባ ስታዲየም 7፡00 ላይ ሲደረግ ሀድያ ሆሳዕና ከነገሌ አርሲ በሀዋሳ ስታዲየም 9፡00 ላይ አርባምንጭ ከተማ ደግሞ ከኢትዮጵያ ቡና 12፡00 ሰዓት ሀዋሳ ላይ ጨዋታቸውን ያካሂዳሉ።
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!



