ባሕር ዳር: ኅዳር 21/2018 ዓ.ም (አሚኮ) በኢትዮጵያ አስተናጋጅነት እየተካሄደ የሚገኘው ከ17 ዓመት በታች የአፍሪካ ዋንጫ የሴካፋ ማጣርያ ውድድር ግማሽ ፍጻሜ ላይ ደርሷል።
በዛሬው የግማሽ ፍጻሜ ጨዋታ አስተናጋጇ ኢትዮጵያ ከኡጋንዳ ጋር ወሳኝ ጨዋታዋን ታደርጋለች።
ኢትዮጵያ ከምድብ አንድ አራት ጨዋታ አድርጋ ሦስቱን በማሸነፍ እና አንዱን አቻ በመለያየት በ10 ነጥብ የምድብ ጨዋታዋን በአንደኝነት ጨርሳ ለግማሽ ፍጻሜ ደርሳለች።
ኢትዮጵያ ዛሬ ተጋጣሚዋን አሸንፋ ለፍጻሜ ለመድረስ ነው የተሻለ ፉክክር እንደምታደርግ የሚጠበቀው።
ወጣት ቡድኑ ባለፉት ባደረጋቸው ጨዋታዎች እንደታየው በማጥቃትም ይሁን በመከላከል የተሻለ ቡድን በመኾኑ የዛሬውን ጨዋታ በአሸናፊነት ያጠናቅቃል ተብሎ ነው የሚገመተው።
በአንጻሩ ተጋጣሚው ኡጋንዳ ከምድብ ሁለት ጨዋታውን በሁለተኛነት ያጠናቀቀ ሲኾን አራት ጨዋታዎችን አድርጎ ሦስቱን ያሸነፈ እና አንዱን ተሸንፎ በ9 ነጥብ ለግማሽ ፍጻሜ መድረስ የቻለ ቡድን ነው።
ቡድኑ ወደ ግብ ክልል ደርሶ ኳስ እና መረብን በማገናኘት በኩል የተሻለ እንደነበር በ18 ንጹህ ግብ ማጠናቀቁ ማሳያ ነው።
በዛሬ ጨዋታም ለተጋጣሚው ኢትዮጵያ ቀላል ቡድን እንደማይኾን ነው የሚጠበቀው። ጨዋታውም በኢትዮጵያ ሰዓት ቀን 9፡00 ላይ ይጀምራል።
ሌላው ዛሬ ቀን 6፡00 ላይ በግማሽ ፍጻሜ የሚገናኙት በምድብ አንድ አራት ጨዋታ አድርጎ አራቱንም በማሸነፍ በ12 ነጥብ ከምድቡ በአንደኛነት ያጠናቀቀው ታንዛኒያ ከምድብ አንድ ከኢትዮጵያ ቀጥሎ ከምድቡ ከአራት ጨዋታ በሦስቱ አሸንፎ አንዱን ተሸንፎ ያጠናቀቀው ኬኒያ ጋር ነው።
ታንዛኒያ እና ኬኒያ በየምድባቸው ካሳዩት ጠንካራ አቋም አንጻር በዛሬው ጨዋታ ሁለቱም ቡድኖች ብርቱ ፉክክር እንደሚያደርጉ ነው የሚጠበቀው።
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!



